በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

75

ሰመራ፣ መስከረም 5/2013(ኢዜአ) በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እንዲውል ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልዩ ልዩ ምግብና ቁሳቁስ ተለገሰ።

ድጋፍ ካደረጉት መካከል የትግራይ ክልል ተወካይ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አረጋዊ እንደገለጹት በሀገር አቀፍ ደረጃ የክረምቱ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው ጎርፍ መጠኑ ቢለያይም በሁሉም አካባቢ ጉዳት እያደረሰ ነው።

አብሮነታቸውንና አጋርነታቸውን ለማሳየት በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ያደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ የክልሉ መንግስትና ህዝብ የላኩትን የተለያዩ ምግብ ነክና ቁሳቁሶች ይዘው በመምጣት መለገሳቸውን ተናግረዋል።

ከለገሱት መካከል ሩዝ፣ ዱቄት፣ ክክ፣ የምግብ ዘይትና አልባሳት እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ ይህም 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት እንዳለው አስታውቀዋል።

ሌላው ድጋፍ ያደረጉት   የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን በበኩላቸው ጎርፍ በአፋር  ወገኖች ላይ ያደረሰውን ጉዳት መመልከታቸውን ገልጸው፤ ተቋሙም አጋርነቱን ለማሳየት የተለያዩ መድኃኒቶችን፣ አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማበርከቱን ተናግረዋል።

"በድር ፋውንዴሽን " የተባለው ድርጅት መሰራች ኡስታዝ በድሩ ሁሴን ድርጅታቸው ከተለያዩ አካላትና አባላቱ ያሰባሰበውን የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች በጎርፍ ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች ይዘው መምጣታቸውን ገልጸዋል።

ከድጋፉም መካከል 750 ኩንታል ዱቁት፣ 100 ኩንታል ሩዝና 10 ሺህ በላይ ሊትር ዘይትና አልባሳት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ጎርፉ ሰዎችን በማፈናቀል ጉዳት ማድረሱን አውስተዋል።

በለማ ሰብልና የቤት እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አመልክተው፤ የክልሉ አመራር እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን  የሚዘልቅ አደረጃጀቶች በማንቀሳቀስ ለተጎጂዎቹ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለመድረስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልልና ሌሎችም አካላት ያደረጉት ድጋፍ ተጎጂዎችን ለማገዝ  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም