በገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች የብልጽግና ጉዞውን እንደሚያፋጥን ተገለጸ

185

ሀዋሳ፣ መስከረም 5 /2013 (ኢዜአ) ገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች በሀገሪቱ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እንደሚያፋጥን በደቡብ ክልል የዳውሮ ዞንና ኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተነደፈው ገበታ ለሃገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት  የሚገኘው በደቡብ ክልል ነው።

የኮንታ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋ የሆኑት ገበታ ለሃገር ፕሮጀክቶች በየአካባቢው ትኩረት ተነፍጓቸው የቆዩ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት ለኢትዮጵያ እድገት የሚበጁ ናቸው። 

ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ልዩ ወረዳው በመጡበት ወቅት በአካባቢው ያለውን የልማት አቅምና ፍላጎት ተረድተው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች አንዱ አካል የሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት ማዘጋጀታቸው በህዝቡ ዘንድ የፈጠረው ደስታና መነቃቃት ወደር የለውም ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆን በመመኘት የወረዳው አመራሮችና የመንግስት ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ መወሰናቸውን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ ሃብት አሰባሳቢ አቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማስተባበር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የልማት ስራው ከሚፈጥረው የስራ ዕድል ባሻገር የአካባቢውን የተፈጥሮ ፀጋ ለዓለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ ለሀገር ገፅታ ግንባታና  እድገት የላቀ  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በለውጡ አመራር እያዳበረ የመጣው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጠረ ጊዜ የመፈጸሙ ተግባር ዜጎችን በሃገር ወዳድነት መንፈስ ለልማት የሚጠበቅባቸውን ተሳትፎ እንዲያበረክቱ ማነሳሳቱንም ጠቁመዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ በዛብህ በበኩላቸው የኮይሻ ፕሮጀክት ለአካባቢው ማህበረሰብ መነቃቃት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተለያዩ ኮሪደሮች የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ሲበቁ ለአካባቢው ህዝብና ለሃገሪቱ እድገት የሚበጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ልማቱ በየአካባቢው እየሰፋ መምጣቱ በመንግስትና ህዝብ መካከል መተማመን በመፍጠር የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እንደሚያፋጥን አስረድተዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ ለፕሮጀክቱ ድጋፍ እንዲሆን የዞኑ የመንግስት ሠራተኞችና አመራሩ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመለገስ ወስነዋል፤ በቀጣይ ነጋዴውና ሌላውም ማህበረሰብ የሚያስተባብር የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ የኮይሻ፣ ጎርጎራና  ወንጪ ሀይቅ አካባቢን በህብረተሰብ ተሳትፎ በማልማት አካባቢዎቹን ተመራጭ የቱሪስት መድረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክቶች ይፋ ማድረጋቸው በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም