ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጋር በአብሮነት ትቆማለች ... ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

62

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4/2013(ኢዜአ) በሱዳን በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ውድመት ያደረሰውን የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሱዳን ሕዝብ ጋር በአብሮነት መቆሟን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “እንደዚህ ዓይነት ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ አዳጋ እንዳይደርስ ከሱዳን መንግሥት ጋር ለመስራት ቁርጠኛ ነን” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሱዳን የሽግግር ሉዓላዊነት ምክር ቤት ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል-ቡርሃን ጋር ሰሞኑን በሀገሪቱ የተከሰተውን ኃይለኛ ዝናብና የጎርፍ መጥለቅለቅ በተመለከተ ትናንት በስልክ መወያየታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት (SUNA) ዘገባ አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁኔታው በቅርቡ ወደ መደበኛ ሁኔታ እንዲመለስ በመመኘት ኢትዮጵያ ለሱዳን መንግስትና ሕዝብ አጋርነታቸውን መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል።

በሌላ በኩል የሱዳን የሽግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶክተር አብዱላ ሀምዱክ ትናንት ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጋር በስልክ ባካሄዱት ዉይይት እርሳቸውም ሆኑ የሱዳን ሕዝብ በሀገሪቱ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች በደረሰው የጎርፍ አደጋ ሰለባ በሆኑት ማዘናቸውን ገልጸዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ አገራቸው የሱዳን መንግሥትና ሕዝብ እንደምትደግፍ ማረጋገጣቸውን በዘገባው ተገልጿል።

ዶክተር ሀምዱክ በበኩላቸው የሶማሊያ ካቢኔ በሶማሊያ የሚገኘውን የሱዳን ነዋሪ ከስደት ክፍያ ነፃ ያደረገው ተነሳሽነት ለሶማሊያ መሪዎችና ሕዝብ ከፍተኛ አድናቆታቸውን መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም