እውቅናና የማዕረግ እድገቱ ለፖሊስ አባላቱ ቀጣይ ስራ ስንቅና ትጥቅ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዳማ ኢዜአ መስከረም 3/2013 የማዕረግ እድገቱ የፖሊስ ሃይሉ የተሰጠውን የክልሉን ሰላምና ጸጥታ በማስፈን የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ በሙሉ አቅሙ እንዲሰራ የሞራል ስንቅና ትጥቅ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልለ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በክልሉ በስነ ምግባርና ሠላምን በዘላቂነት በማስፈን ረገድ ወሳኝ ሚና ለነበራቸው አባላት የእውቅናና ማእረግ እድገት ሰጥቷል።

በአዳማ በአባ ገዳ አዳራሽ በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ  ከረዳት ሳጂን እስከ ምክትል ኮሚሽነር የማዕረግ እድገት ተሰጥቷል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል አራርሳ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዛሬ የተሰጠው እውቅናና የማዕረግ እድገት በክልሉ ሰላምን ይበልጥ ለማረጋገጥ ያላው ሚና የጎላ ነው።

በተለይም በመልካም ስነ ምግባር የታነጸና በስራቸው አርአያ ለሆኑ አባላትና በረዳት ኮሚሽነርነት ረጅም አገልግሎት ለሰጡት አመራሮች ማዕረጉ እንደተሰጠ ተናግረዋል።

ዛሬ "የማዕረግ እድገት የስራ ውጤት ማሳያ" በሚል መሪ ሐሳብ የተሰጠው እውቅናና የማእረግ እድገት እውነትም የስራ ውጤት መሆኑን ያሳያል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ባለፈው በጀት ዓመት የክልሉ ፖሊስ ከውስጥና ከውጭ የተቃጣውን የጥፋት ሃይሎች ተልዕኮ በማክሸፍ እንዲሁም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በብቃት መወጣታቸውን አመላካች ነው ብለዋል።

የተሰጠው እውቅናና ማዕረግም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን በሚደረገው የፖሊስ የእለት ተለት ተልዕኮ ቀጣይ ስራ ውጤታማነት ጭምር የታለመ መሆኑን አመልክተዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ለአባላቱ እውቅናና የእድገት ማዕረጉን የሰጡት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የኦሮሚያ ፖሊስ ሃይል ለክልሉ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም በ2012 ክልሉን ለማመስና የሁከትና ብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ የተሸረበውን ሴራ በመበጣጠስ አኩሪ ገድል የፈጸሙ የህዝብ ጋሻና መከታ የሆነ ሃይል መፈጠሩንም ተናግረዋል።

የማዕረግ እድገቱ የፖሊስ ሃይሉ በልዩ ሁኔታ የተሰጠውን የክልሉን ሰላምና ጸጥታ በማስፈን የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በሙሉ አቅሙ ጭምር እንድሰራ የሞራል ስንቅና ትጥቅ መሆኑንም አመልክተዋል።

በቀጣይነትም ሁሉም አባላት በመልካም ስነምግባርና ህገ መንግስታዊ ታማኝነታቸውን በመጠበቅ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

በዚህም አስተማማኝ ሰላም በዘላቂነት በማስፈን የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ እንደ ወትሮው ከህዝብ ጋር በመሆን በሙሉ አቅም መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ዛሬ የማእረግ እድገቱ የተሰጣቸው 4 ሺህ በላይ ሲሆኑ በነበራቸው ተሳትፎ በአገልግሎታቸውና በሌሎችም መስፈርቶች ከረዳት ሳጅንነት እስከ ምክትል ኮሚሽነርነት የማዕረግ እድገት አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም