"ዘመኑ ሲለወጥ አብረን እንለወጥ"

59

"ዘመኑ ሲለወጥ አብረን እንለወጥ" በብርሃኑ ተሰማ (ኢዜአ)

የሕይወታችንን አንዱን ክፍል በዘመን መለኪያ ሰፍረን አንድ ዓመት ጨርሰን ወደ ሌላው ተሻግረናል።እንኳን ለ2013 አዲስ ዓመት አደረሰን!!!


2012 ታሪክ ሆኖ ላይመለስ ሄዷል፤ አዲሱ ዓመትም ከ365 ቀናት በኋላ ይህንኑ ይጋራና ያልፋል።ዘመን ዘመንን እየተካ፤ዛሬ ትናንት፤ ነገ ደግሞ ዛሬን እየተካ ይቀጥላል።


ለሁላችንም እኩል በተሰጠው ጊዜ በሚያልፍ ጊዜ የማያልፍ ታሪክ ለመስራት ምን እንዳደረግን ራሳችንን እየጠየቅን ዘመንን በዘመን ተክተናል።


ያለፈው ዓመት በርካታ መልካም ነገሮች የተስተዋሉበት የነበረ ቢሆንም በዚያው ልክ በርካታ ፈተናዎች የነበሩበትም ነበር።

በመሆኑም አዲሱን ዓመት ስንቀበል ካለፈው ዓመት የማንወርሳቸውን ‘’የታሪክ ጠባሳዎችን" ላለማሻገር ቃል ገብተን "አድሱን ዓመት ስንቀበል እኛም ታድሰን" መሆን ይኖርበታል።

ዓመቱ ሲታደስ እኛም አእምሯችንን አዲሰን ካልተቀበልነው "የቆየ ወይን በአዲስ አቁማዳ" ስለሚሆን መያዣው አዲስ ቢሆንም ወይኑ የጣእም ለውጥ አይኖረውም ማለት ነው።

ሽልማቶቻችን


ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍ ያደረገና ማንም ኢትዮጵያዊ አግኘቶት የማያውቀውን ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በዓለም ታላቁ የተባለውን የኖቤል ሰላም ሽልማት ባለቤት ሆነዋል።


ሽልማቱ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ክስተት ሲሆን የአገራችንን ስም በዓለም አደባባይ በስፋት ያስተዋወቀ ነበር። "ታላቁ ሽልማት ዳግም ታላቅ አድርጎናል" ያሉም በርካቶች ነበሩ።


የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት መከናወኑ የፈጠረው ደስታም ወደር አልነበረውም።

የዘመናት ቁጭት፣ የባለቤትነት፣ የአሸናፊነትና የወደፊት ዕድገት ተስፋ የተንጸባረቀበት ደስታችን ወረርሽኙ ሳይበግረው በአደባባይ የታየበት ዓመት እንድናሳልፍ ያደረገበት ዓመት 2012 ነበር።


በግድቡ ጉዳይ ከግብዕና ከሱዳን ጋር የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር አድካሚና የተለያዩ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ያስተናገደም ነበር። ወደ ፊት የሚካሄደው ድርድር ግን ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት የተካሄደው ዓይነት እንደማይሆን አስተምሮን አልፏል።


ኢትዮጵያ በወንዙ ባላት ባለቤትነት በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቃሚ የሚያደርጋትን ሥራ በሐምሌ አጋማሽ ባደረገችው የውሃ ሙሌት አረጋግጣለች። በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ የሚደረገውን ግንኙነት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ በመያዝ ሃይል ለማመንጨት እየተንደረደረች ትገኛለች።

ግድቡ ሲጠናቀቅ 74 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ አከማችቶ ኤሌክትሪክ በማመንጨት ኢትዮጵያዊያንንና የአካባቢውን አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደረግ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋን መረጃ ሰጭ ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተ ነበር።


ኢትረስ-1 የተባለችውና 72 ኪሎ ግራም የምትመዝነው ሳተላይት ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃና ለመልክዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎት መስጠቷን ጀምራለች።


ዓለምን ያሳቀቀው ክስተት


ያሳለፍነው ዓመት ዓለማችንን ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ ችግር ያየችበት ነበር። ሰንኮፉ ሳይነቀልም ወደ ቀጣዩ ዓመት ገብተናል። የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ 19 ብሎ የሰየመው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምድራችንን አርዶታል።

እስካሁን ከ25 ሚሊዮን በላይ የዓለም ህዝቦች በበሽታው ሲያዙ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችም በወረርሽኙ ህይወታቸው አልፏል።

ከትንሽ እስከ አዋቂ፤ ደሃ ሳይል ሃብታም እኩል ያስጨነቀው ኮቪድ 19 አሁንም መዛመቱን እንደቀጠለ ይገኛል።

ይሄንን ዓመት አጠናቀን ወደ ቀጣዩ ዓመት ስንሸጋገር ዓለማችንን ቀስፎ የያዛት ከ100 ዓመታት በኋላ በተባለ ክስተት የኮሮናቫይረስ ስጋት ሳትላቀቅ ቀጥላለች።

የኮሮናቫይረስ በቻይና ውሃን ሲከሰት እምብዛም አያሰጋም በሚል "ተንቆ" ቆይቶ የኋላ ኋላ ግን ዓለምን "አሳቅቋል"።

ሲጀመር ሩቅ መስሎ ታይቶ ዓለም ለማዳረስ ሳምንታት ነበር የፈጀበት።


የዓለም መሪዎች ‘’ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አጋጥሞ የማያውቅ’’፣’’ከቫይረሱ ጋር ጦርነት ገጥመናል’’ ሲሉ ተናግረዋል።

የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ጉድለትና እጥረት እንዲሁም በሐኪሞች ላይ የሥራ ጫና መብዛት ኮቪድ 19ን ፈታኝ አድርጎታል። ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በሰው ልጆች ላይ የገጠመ ሌላኛው ‘’ክፉ ቀን’’ ተብሎም በታሪክ ተመዝግቧል።


ወረርሽኙ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያደረሰው ጉዳት የትየለሌ ነው።ፖለቲካዊ ትርምሱና ማህበራዊ ቀውሱም ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም።እንዲያው በደፈናው ዘመኑን የማይመጥን ዱብዳ ሆኖ እስካሁንም ቀጥሏል።


ወረርሽኙና አዲሱ ሕይወት 


የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያም ጫናው ከባድ ነበር። የወረርሽኙ መከሰት ከኢኮኖሚው ጫናው በተጨማሪ በዜጎች ላይ የፈጠረው ሥነ ልቡናዊ ቀውስም ቀላል አልነበረም።


በኢትዮጵያ መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የቫይረሱ መገኘት ከተረጋገጠበት እለት አንስቶ እስካሁንም በርካቶችን እያዳረሰ ይገኛል።


በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ምርምራ ውጤቱን ለማወቅ ደቡብ አፍሪካ የምትልከው፣የእጅ ንጽህናን ለመጠበቅና የአፍና አፍንጫ መሸፈናዎችን ከውጭ ታስገባ የነበረችው አገር ሁኔታዎችን ለመቀየር የወሰደባት ከሁለት ወራት ያልበለጠ ነበር።


በአዲስ አበባና በክልል ታላላቅ ከተሞች ለይቶ ማቆሚያዎችና ማገገሚያ ማዕከላትን ለማቋቋም የወሰደው ጊዜም አጭር ነበር። የጤና ባለሙያዎች ራሳቸውንና ሕዝቡን ከወረርሽኙ ለመታደግ ያደረጉት ዝግጅትም የሚያኮራ ነበር።


በኢትዮጵያ አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ50 ሺህ ሲያልፍ የሟቾችም ቁጥር 900 ደርሷል።

ሆኖም የማህበረሰቡ ጥንቃቄና መከላከል እየተቀዛቀዘ መምጣቱ የቫይረሱን ስርጭት ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል።

ቫይረሱ የእያንዳንዱን ቤት እስከሚያንኳኳ ድረስ መጠበቅ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ አሁንም "ሳይቃጠል በቅጠል" በማለት መንግስትና የጤና ባለሙያዎች ውትወታቸውን ቀጥለዋል።


መንግሥት 17 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመርመር ያስተላለፈው ውሳኔና አተገባበሩም የባህርይ ለውጥ እንደሚያመጣና ጉዳቱን ለመቀነስ እንደሚያስችል ይታመናል።ኮሮናን የምንቆጣጠረው እንጂ፤ የሚቆጣጠረን እንደማይሆን በዓመቱ ማገባደጃ ላይ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ተስፋ ይሰጡናል።


የአገሪቱ የትምህርት ተቋማት ከሁለተኛው ወሰነ ትምህርት ጀምሮ በወረርሽኙ ምክንያት በመዘጋታቸው ይታወቃል። ትምህርትን በኢንተርኔት፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ለመስጠት ጥረት የተሟላ ትምህርት ለመስጠት የተቸገርንበትን ዓመት አሳልፈናል።


‘’ማዕድ ማጋራት’’


የቫይረሱን መስፋፋት ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረው የ’’ማዕድ ማጋራት’’ መርሐ ግብር ወገን ወገኑን የሚደግፍበት ቅን ልብ መኖሩን በተግባር አሳይቷል።

ከምግብ እስከ ንጽህና ቁሳቁስ የተደረገው ልገሳ የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ ሳይገታቸው ባለሀብቶች ካላቸው አካፍለዋል። ወገን ወገኑን ባለው በመደገፍ በመረዳዳትና በመደጋገፍ እንደምንኖር አስመስክሯል።


በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቋማት ጤና ተቋማትን ሳይቀር ደግፈዋል። በጎደለ ሞልተዋል። በተለይ በአሜሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሥራ አጥተውና ለወረርሽኙ ተጋልጠው እያሉ አገር ውስጥ ያለውን ወገናቸውን ለመርዳት ያሳዩት ተነሳሽነት የሚያስደንቅ ነበር።


አገርንና ለውጡን መሞገት 

ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል በአገሪቱ የመጣው ለውጥ በራሱ ‘’ለውጥ’’ን ሲፈራ አላየሁም። ለውጡ አገር የሚያፈርስና ሕዝብን ለመበታተን ለተነሱ ኃይሎች አልመጣምና በዚያ መሥመር የመጡትን ለማስተናገድ ሲቸገር ነበር። እንዲያውም አመራሩ ባሳየው ትዕግሥትና ሆደ ሰፊነት ብዙዎች ተጎድተዋል። ንብረትም ወድሟል። የመንግሥት ህግ እንዲያስከብር የሚወተውቱ ዜጎች ቁጥርም ቀላል አልነበረም።


ዓመቱ ለውጡን ወደ ራሳቸው መንገድ ለመውሰድ በሞከሩ ጽንፈኞችና አክራሪ ብሄርተኞች ጥፋት ተፈጽሟል። በድርጊቱ ሕዝብን ከህዝብ ለመከፋፈል የተደረገው ሙከራም አልተሳካም።


በሂደቱ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የወሰደው እርምጃ ሰላምና መረጋጋትን አምጥቷል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ችግር ዳግም እንዳይከሰት ሕጋዊና አስተማሪ እርምጃዎች መውሰድ በማስፈለጉ ይሄው ተደርጎ ችግሩ እልባት አግኝቷል።


መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሕግ የበላይነትን የማስከበርና የማረጋገጥ ተግባር ‘’በዚህ ይብቃ’’ ብሎ መነሳቱ አገሪቱን ከጥፋት ያዳነ ነበር። 


የአገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ 2012ን እንዲሻገር መደረጉ ሌላው የዓመቱ መገለጫ ሆኖ አልፏል። የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውጭ በራሱ ምርጫ ለማካሄድ የተንቀሳቀሰበት አጋጣሚም በበርካቶች ትዝብት ላይ የወደቀ ክስተት ነበር።

የክልሉ ገዥ ፓርቲ ራሱ ደጋሽ፣ ራሱ ታዛቢ፣ ራሱ መራጭና አስመራጭ በመሆን የተወነው ድራማ የተለየ ውጤት ያልመጣበት ትርፉ ወጭ ብቻ ሆኖ አልፏል።

ደቡብና ጥያቄዎቹ 


የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች ውሳኔ ያስተላለፋል ተብሎ ሲጠበቅ ዓመቱ ተጠናቋል። የምክር ቤቱን ውሳኔ ለመጠበቅ ያላስቻላቸው ዞኖች ተከስተዋል። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በተለይ በደቡብ ክልል የሚነሱ ጥያቄዎችን ማንነትን ባልካደና ኢትዮጵያዊነትን ባስከበረ መልኩ ለመፈጸም እንደሚሰራ አረጋግጧል።


በዚህ ዘመን የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በጥናት ላይ ተመስርቶ እንጂ፤ ባልተረጋጋ ሁኔታ በግርግር መሆን እንደማይገባው መንግስት ያምናል። መጀመሪያ የአገር ሰላምና መረጋጋት ይፈጠር። ’’ዛሬ ካልሆነ’’ብሎ መገኘት ግን ለማንም አይጠቅምም። በዚህ ላይ የዚህችን አገር የወደፊት አከላከል ለመወሰን የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ጉዳይ በኮሚሽን እየታየ መሆኑን ማወቅ ተገቢነት አለው።

ኢኮኖሚው 


ዓመቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ከአምስት ዓመታት በኋላ 3 ቢሊዮን ዶላር ያለፈበትን አፈጻጸም አይቷል።


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ዓቢይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት የአገሪቱ ዓመታዊ ጥቅል ምርት 3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ብር መድረሱንም ይፋ አድርገዋል። ከሁለት ዓመታት በፊት አገራዊ ጥቅል ምርቱ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ነበር።


ለግል ዘርፍ የሚመደበውም ብድር ከ90 ቢሊዮን ብር ወደ 160 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም አስታውቀዋል።


የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በተለይ ባንኮች በተቀማጭ፤ በቁጠባና በብድር የሚሰጡት አገልግሎት ዕድገት ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። በዓመቱ ውስጥ 12 ያህል ባንኮች በምስረታ ሂደት ነበሩ። የተወሰኑት በአገሪቱ የመጀመሪያዎቹ እስላማዊ ባንኮች ሆነው ሥራ እንደሚጀምሩም ይጠበቃል። 

የአገሪቱ ሁሉም የንግድ ባንኮች 87 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ሲያደርጉ፣ የሰጡት ብድር 221 ቢሊዮን ደርሷል፣ እንዲሁም በተበዳሪዎች ላይ የነበራቸው 138 ቢሊዮን ብር ብድር ተመልሶላቸዋል። ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ብልጫ የተመዘገበበት ዘመን እንዳሳለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አስታውቀዋል።

በየኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበላሸ ብድር ወደ ሁለት በመቶ ወርዷል። በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያልተመለሰ ብድር 34 ከመቶ ቢሆንም፤ ከ2011 ተመሳሳይ ወቅት የ13 በመቶ በመቀነስ መሻሻል ታይቶበታል ብለዋል።


ከቡና የወጪ ንግድ 667 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።ይህም ከዕቅዱ16 በመቶ ብልጫ አለው። ከአበባ ምርት የተገኘው 440 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘበት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስተሩ ገልጸዋል።

ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የሆነው 800 ኪሎ ግራም ወርቅ ከአምስት ዓመታት በኋላ የተሻለ ውጤት የተመዘገበበት ዓመትም ሆኖ ተመዝግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ባንኮች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ቦንድ እንዲገዙ ከተቀመጫቸው 27 በመቶ የሚይዝበትን አሰራር ማስቀረቱ በተሻለ መልኩ ለመንቀሳቀስ አስችሏቸዋልም ብለዋክል። ውዝፍ ግብር ለነበረባቸው ነጋዴዎች 78 ሚሊዮን ብር ዕዳ መሰረዙንም አስታውቀዋል። 


ኮሮናን እየተከላከሉ ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ የተደረገው ጥረት በግብርናው ዘርፍ ያልታረሰ መሬት ጭምር ጥቅም ላይ በማዋል በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን እንቅስቃሴ በደገፈ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። 

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ስጋት የነበረውን የበረሃ አንበጣን በመከላከል ረገድም 95 በመቶ ውጤታማ መሆን ተችሏል።


በአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው ዕቅድም በስኬት ተደምድሟል።

2013 ምን ይዞልን መጣ?

ዘመንን ጥሩም መጥፎም የምናደርገው እኛው ነን። እርግጥ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ነገሮች የሚለውጡት ነገር ይኖራል። አዲስ በምንቀበለው ዓመት ከምንም በላይ የምንፈለግውና ልናሳካው የምንችለው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን ዜጎቿ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው የሚኖሩባት፣የሚሰሩባትና የሚኮሩባት አገር ባለቤት መሆንን ነው።


ፖለቲካዊ 


አገሪቱ እየገነባችው ያለው የመድብለ ፓርቲ ግንባታ ሥርዓት ምህዳሩን እንድታሰፋ ያስገድዳታል። በአገርና በክልል ደረጃ ባለፈው ዓመት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተስተጓጎለው ምርጫ ተካሂዶ ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ብሎም ተዓሚነት ያለው ሆኖ የሕዝብ ድምፅ የሚሰማባቸው ምክር ቤቶች አባላት ይመረጣሉ የሚል እምነት ተሰንቋል።

የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጡ ተግባራርም በተሻለ መልኩ ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።


ኢኮኖሚያዊ 


ከአዲሱ ዓመት እስከ 2022 የሚተገበረው የ10 መሪ የልማት ዕቅድ ትግበራዊነቱ ይጀመራል። ዕቅዱ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም በማስመዝገብ የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ እንደሚያሻሽል ተስፋ ተጥሎበታል።


አገራዊው መርሃ ግብር ‘’ኢትዮጵያ፤ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት’’ በሚል እሳቤ የሚከወን ሲሆን ዕቅዱ አገሪቱ በ2011 ያፀደቀችውን ‘’ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ’’ መነሻ ያደረገ ነው። 


አጀንዳው‘’የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ማበልጸግ’’ን ዓላማው ያደረገ መርሃ ግብር ነው።


በፕላንና ልማት ኮሚሽን አማካይነት የሚተገበረው መርሃ ግብር በዋነኝነት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ለማሻሻል ተሰናድቷል። በዚህም መርሃ ግብር ባለፉት ዓመታት የተገኘውን ስኬት ላይ በመመስረት ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል።

ዓለም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተላምዶ መኖርን ስለሚቀጥል ተማሪዎችና መምህራን ቤት መዋላቸው ይቀራል ተብሎ ይጠበቃል። ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ የወረርሽኙን መከላከያ መንገዶች መተግበር ግድ ማለቱ አይቀርም። ለወረርሽኙ መድኃኒት ወይም ክትባት እስኪገኝለት ድረስ ህይወትን በጥንቃቄ ማስቀጠል ግድ ይላል።


ሕዝቡ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያለው ተነሳሽነትና ግንዛቤ ዕድገት መጠናከሩ የማይቀር ነው። በዚህም የፍትህ አካላትና የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ተቅማት ሚናም እየጎለበተ መሄዱ ተጠባቂ ጉዳይ ነው። መረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልም እንደሚጠናከር ይጠበቃል።

በአዲሱ ዓመት


አንዱን ዘመን አጠናቀን ወደ ሌላው ተሸጋግረናል። በዕድሜያችን አንድ እንጨምራለን። በዚያው ልክ አገርም ወደ ፊት እንድትራመድ በሚያልፈው ዕድሜያችን ጠቃሚ ሥራዎችን ማከናወንይጠበቅብናል። እናም በ2013 አዲሱን ዓመት በአዲስ መንፈስ ተቀብለን የተሻለች አገር ለመገንባት መነሳት ይጠበቅብናል።


አዲሱን ዓመት ስንቀበል ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ ታላቅ አገር መሆኗን በመረዳት መገፋፋትን፣ መነቋቆርን፣ ጠብንና ጥላቻን አስወግደን አብረን በፍቅር ለመኖር መሆን ይኖርበታል።


በግጭት መጎዳዳት ብሎም አገርን ማፍረስ ቢሆን እንጂ አንዳችም የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን መካሪ አያስፈልግም።

በሻሸመኔ እና መሰል ከተሞች የደረሰው ውድመት ኪሳራ ላይ ጣለን እንጂ ትርፍ አላገኘንበትም። በነበረው ግጭት በርካታ ንብረት ወድሟል፣ ብዙዎችን ያለ ቤት አስቀርቷል፣ ስራ በማሳጣትም የእለት ጉርስ ከጃይ አድርጓቸዋል።

አርስ በእርሳችን ገዳይና ተገዳይ፣ አንዱ አፍራሽ ሌላው ገንቢ ሆነን በመጓተት አገራችንን ከማፍረስ ተቆጥበን ለበልጽግናዋ በጋራ ልንሰራ ይገባናል።

ዓመቱ ሲታደስ እኛም አብረን ታድሰን አገራችንን በጋራ እናልማ፤ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት ለሁላችን። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

መልካም አዲስ ዓመት!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም