በኢትዮጵያ ብዙ የቱርክ ዜጎችን ማየት እንፈልጋለን – — የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል

229

መስከረም 2/2013(ኢዜአ) የቱርክ ዜጎች ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ማየትና ከቡና መገኛ ምድር የቡና ጣዕሙን እንዲያጣጥሙ ፍላጎታቸው መሆኑን በኢስታንቡል የኢትዮጵያ ተጠባባቂ ቆንስላ ጄኔራል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ተጠባባቂ ቆንስላ ጄኔራል ወይዘሮ እፀገነት ይመኑ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ለቱርክ ዜና አገልግሎት ለአናዶሉ እንደተናገሩት  አዲስ አበባ ‘ከወዳጅ ሀገር ቱርክ ለመጡ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን’ ትፈልጋለች፡፡

“በቱርክ አዲሱን ዓመት ለማክበር የእኔ የግል ተሞክሮ ከቀድሞዎቹ በጣም የተለየ ነው፣ ምክንያቱም ጠንካራ ማኅበረሰብ ወይም የተለያዩ የኢትዮጵያ ምግብ ቤቶች የሉም” በማለት ለአናዶሉ ኤጄንሲ በስልክ ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

ወይዘሮ እፀገነት እንደተናገሩት በተለምዶ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል በኢትዮጵያ ውስጥ የቤተሰብና የጓደኞች መሰባሰብን የሚያካትቱ ልዩ አጋጣሚዎች ናቸው።

“ግን በዚህ ዓመት በ COVID-19 ምክንያት ይህንን ማድረግ አንችልም” ነው ያሉት።

አያይዘውም አዲሱን ዓመት ከባህር ማዶ ሆኖ ማክበሩም ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።

ወይዘሮ እፀገነት ቱርክና ኢትዮጵያ ብዙ ተመሣሣይነት እንዳላቸው በመግለጽ በሁለቱ አገራት መካከል ቀጥታ በረራዎች የሚከናወኑት በኢትዮጵያና በቱርክ አየር መንገዶች ነው።

ሀገሪቱ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከአንድ ሺህ ዓመት ገደማ በፊት ያፈራችውን ቡና በመጥቀስ “ብዙ የቱርክ ዜጎች አገሬን ሲጎበኙና ቡናውን ከትውልድ አገሩ ሲቀምሱ ማየት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ቆንስላ ጄኔራሏ በኢትዮጵያ ስላለው ተስፋ ተጠይቀው “በ2013 ለኢትዮጵያውያን የሰላምና የብልፅግና ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚከናወኑ የአጭር ጊዜ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ማየት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

በተጨማሪም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር ውሎ ሁሉም ሰው ከዚህ በፊት ወደ ነበረው ሕይወት እንደሚመለስ ተስፋቸውን ገልጸዋል።