ለተቸገሩ ወገኖች ለበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ

76

ጎንደር፣ወልዲያ፣ ደብረ ብርሃን፣ መስከረም 2/2013 (ኢዜአ) በጎንደር፣ ወልዲያና ደብረ ብርሃን ከተሞች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ከ800 ለሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ለበዓል መዋያ ድጋፍ ተደረገ።

በጎንደር ከተማ ከባለሀብቶችና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተገኘ ግማሽ ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፉ 220 ለሚሆኑ የደሃ ደሃ  ወገኖች ተለግሷል።

ከድጋፉም መካከል  ዶሮ፣ እንቁላል፤ የዳቦ ዱቄትና የምግብ ዘይት ይገኙበታል።

የከተማዋ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ማስተዋል ስዩም በድጋፉ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ወቅት እንዳሉት መረዳዳትና መተሳሰብ ዘመናት የተሻገረ የኢትዮጵያዊነት በጎ እሴታችን  ነው፡፡

ለተቸገሩ ወገኖች የበዓል መዋያ ስጦታ መደረጉ ኃይማኖታዊ ስርዓቱ የሚደግፈው በጎ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ስራአስኪያጅ ሊቀ-ህሩያን አባ ዮሴፍ ደስታ ናቸው፡፡

አዲሱ ዓመት የሰላም ፣የደስታና የብልጽግና ዘመን እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በከተማው የቀበሌ 13 ነዋሪ ወይዘሮ ንግስት እንዳለ  በሰጡት አስተያየተ በሰው ቤት እንጀራ በመጋገር ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እንደሚገፉ ጠቅሰው ለበዓል መዋያ በተደረገላቸው ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የ33ኛ ክፍለ ጦር የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጎንደር ከተማ ለሚገኙ 100 ለሚደርሱ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ወገኖች ለበዓል መዋያ የምግብ ድጋፍ አድርገዋል።

የክፍለ ጦሩ ዋና አዛዥ ኮሎኔል ደስታ ተመስገን ድጋፉን በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት ሰራዊቱ ድጋፉን ያደረገው ከወር ደመወዝ በመቀንስ ነው፡፡

አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግም ሰራዊቱ 131ሽህ  ብር በማዋጣት 50 ኩንታል ዱቄትና 300 ሊትር የምግብ ዘይት ገዝቶ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡

በሌላም በኩል የጎንደር ከተማ ጫኝና አውራጅ ማህበር 30 ለሚደርሱ አካል ጉዳተኞች ለእያንዳንዳቸው ለበዓል መዋያ 200 ብር እንዲሁም ለአንድ የአረጋውያን መርጃ ማህበር ደግሞ 14ሺ ብር በጥሬ ገንዘብ ለግሷል።

በተመሳሳይ የዳሽን ቢራ አክሲዮን ማህበር በወልድያ ከተማ ለሚገኙ 200 አቅመ ደካሞች የዳቦ ዱቄት፣ ዘይትና ፓስታ ድጋፍ አደርጓል።

የማህበሩ የወልድያ ተጠሪ አቶ ሰሎሞን አረጋዊ ድጋፉ አቅመ ደካሞችና ጧሪ የሌላቸው አረጋውያን የተደረገ መሆኑን አመልክተው ይህም የ178 ሺህ ብር ግምት ያለው ነው ብለዋል።

የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ መሐመድ ያሲን በበኩላቸው በኮሮና ምክንያት ብዛት ያላቸው ዜጎች ለችግር ተጋልጠው እንደቆዩ ገልጸው ፤ችግሩን ለመቋቋም እንዲያግዝ ሃብት በማሰባሰብ የመደገፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የዳሽን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር በደብረ በርሃን ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 300 ወገኖች የበዓል መዋያ 264 ሺህ ብር ግምት ያለው ድጋፍ አድርጓል።

የፋብሪካው ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታነህ ዝቄ እንደገለጹት በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የዘመን መለወጫ በዓልን ተደስተው እንዲያሳልፉ ድጋፉ ተደርጓል።

ድጋፉም 62 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣  አንድ ሺህ 500 ሊትር የምግብ ዘይት እና 70 ካርቶን ፓስታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም