ኢትዮጵያ በዲጂታል ክፍያና መታወቂያ ፕሮጀክት ላይ ለምትሰራቸው ስራዎች ማስተርካርድ ድጋፍ ሊያደርግ ነው

83

አዲስ አበባ፣ ጷጉሜን 5/2012 (ኢዜአ) የአሜሪካው የፋይናንስ አገልግሎት ተቋም ማስተርካርድ፤ ኢትዮጵያ በዲጂታል ክፍያና የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት ላይ ለምትሰራቸው የቴክኖሎጂና የቴክኒክ ድጋፍ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ያሳድጋል ተብሎ የታመነበት የመግባቢያ ሰነድ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና በማስተርካርድ መካከል ዛሬ ተፈርሟል።

ሥምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) እና የማስተርካርድ ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ፕሬዝዳንት ራግሐቭ ፕራሳድ ተፈራርመዋል።

ሁለቱ አካላት አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ አነስተኛ የንግድ ተቋማትን ለመደገፍ እንዲሁም የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ዝግጁነትን ለማጎልበት የሚያስችሉ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና አማራጮችን ለመጀመርና ለመተግበር የሚያስችል ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ተስማምተዋል።

ሥምምነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ ልዩ ቴክኖሎጂዎችን ለተለያዩ አገልግሎቶች በማዋልና በመተግበር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳውን ዕውን ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በማስተርካርድ በኩል በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሀገራትን ልምድና ተሞክሮውን በመጠቀም ኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ረገድ የተቀመጡ ግቦች እንድታሳካ እገዛ እንደሚያድርግ ተገልጿል።

በሥምምነቱ መሠረት ማስተርካርድ አካታች የፋይናንስ ሥርዓትን ለማስፈን፣ ለአነስተኛ የንግድ ተቋማት አስተማማኝና ቀላል የዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክቶች ለመተግበር ለተጀመሩ ጥረቶች ቀጥተኛ ድጋፍ ያደርጋል።

ድጋፉ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎችን መትከል፣ የሥልጠናና የአቅም ግንባታ ለባለሙያዎች መስጠትና የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማቅረብ እንደሆነ ተገልጿል።

ማስተርካርድ በሌሎች አገራት ያለውን ተሞክሮ ወደ ኢትዮጵያ ይዞ እንደሚመጣና በአገልግሎቶቹ ላይ ችግር ሲፈጠር መፍትሔ የመስጠት ተግባር ያከናውናል።

በሚቀርበው የፋይናንስ አገልግሎት ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የታቀደ ሲሆን አጠቃላይ ድጋፎቹ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ።

የድጋፍ ማዕቀፉ የዲጂታል ስትራቴጂው ትግበራን በማከለ መልኩ የሚሰጥ እንደሆነና ደረጃ በደረጃ የሚከናወን መሆኑ ተመልክቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አህመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ሥምምነቱ ጥቃቅንና አነስተኛ ነጋዴዎች የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትና ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም ከመላው ዓለም ጋር እንዲገናኙና ክፍያዎችን ዲጂታል በሆነ መንገድ መቀበል እንዲችሉ የሚያደርጋቸው ነው ብለዋል።

በሥምምነቱ የሚሰሩ ሥራዎች በኢትዮጵያ በጥሬ ገንዘብ ከሚፈጸም ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ወጪዎችን ለመታደግ እንዲሁም ከሕጋዊው ሥርዓት ውጪ የሆኑ የገንዘብ ልውውጦችን እንደሚያስቀሩ ገልጸዋል።

ሰዎች ካርድን እንደ ገንዘብ ተጠቅመው የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን መጠቀማቸው የፋይናንስ ተደራሽነትን የሚያሰፋ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።

ወደ ትግበራ የገባውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ለማስፈጸም እንደሚያግዝም አመልክተዋል።

ከማስተርካርድ ጋር የሚኖረው ትብብር መሠረተ ልማት ለማጠናከር ዲጂታል የልውውጥ ሥርዓቶችን በመንግሥት፣ በግሉ ዘርፍና በዜጎች መካከል ለማስፈን እንዲቻል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የማስተርካርድ ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ፕሬዚዳንት ራግሐቭ ፕራሳድ በበኩላቸው ድርጅታቸው ከመንግሥት ጋር በመሆን በዲጂታል ስትራቴጂው የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት እንደሚሠራ ገልጸዋል።


ሥምምነቱ ኩባንያው አንድ ቢሊዮን ሰዎችንና 50 ሚሊዮን ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን እ.አ.አ በ2025 ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማምጣት የያዘነውን ግብ ለማሳካት የሚረዳ ነው ብለዋል።

ማስተርካርድ የፋይናንስ ልውውጦች አስተማማኝ፣ ቀላልና ተደራሽ በማድረግ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ማስተርካርድ በኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማስፈን የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ተጣምረው እንደሚሰሩ የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰኔ 2012 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱንም አውስቷል።

ማስተርካርድ በሚያዚያ 2012 ዓ.ም ለስትራቴጂው ትግበራ የ600 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ለስትራቴጂው መቀረጽ የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም