ባንኮች ከሚሰጡት ዓመታዊ ብድር አምስት በመቶውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ ብድር እንዲያውሉ መመሪያ ወጣ

አዲስ አበባ፣ ጷጉሜን 5/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ከሚሰጡት ዓመታዊ ብድር አምስት በመቶውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ ብድር እንዲያውሉ የሚያስገድድበት መመሪያ ይፋ ሆነ።

ባንኩ ይፋ ያደረጋቸው መመሪያዎች ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዞ መበደር ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ለአነስተኛ ኢንሹራንስ ሥራ ፈቃድ መስጠትና ምዝገባ መመሪያ አርሶ አደሮቹ ለሚያስዙት ብድር ዋስትና እንደሚሰጥበት ተገልጿል።

ባንኩ በመመሪያዎቹ ላይ ከፋይናንሱ ዘርፍ አካላት ጋር ትናንት ውይይት አድርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በመመሪያዎቹ ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ለዋስትና ማስያዣ የሚሆኑት ንብረቶች ተመን አወጣጥ፣ የተንቀሳቃሽ ንብረት ምዝገባና የኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት በዋስትና አሰጣጥ ባላቸው ሚናና መመሪያዎችን በሚተገበሩበት የፋይናንስ አቅም ዙሪያ ሀሳቦች ተሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዞ መበደር መመሪያ በ2011 ዓ.ም ተግባራዊ በሆነው ተንቀሳቃሽ ንብረት እንደ ዋስትና ማስያዝ የሚያስችለውን አዋጅ ለመተግበር መውጣቱን ገልጸዋል።

በመመሪያው መሠረት ባንኮች በዓመት ውስጥ ከሚያበድሩት ገንዘብ አምስት በመቶውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ የብድር ዓይነት እንዲያውሉ ያስገድዳል ብለዋል።

የብድሩ አቅርቦት የፋይናንስ ተደራሽነት የማሳደግና የተበዳሪዎችን መጠን ከመጨመር አኳያ ያለው ፋይዳ መሆኑን ተናግረዋል።

ብድሩ በተጨማሪ አርሶ አደሮች የፋይናንስ ሀብት አግኝተው ምርታማነታቸውን መጨመር እንደሚያስችላቸው የገለጹት ዶክተር ይናገር ለተያዘው ንብረት ዋስትና የሚሰጠውም መመሪያም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ያለው ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

ባንኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካወጣቸው 47 መመሪያዎች ውስጥ ሁለቱ መመሪያዎች ለኅብረተሰቡ የሚጠቅሙ ናቸው ብለዋል።

በአጠቃላይ ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና አስይዞ መበደር መመሪያ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን፣ የፈጠራ ባለሙያዎችንና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ የብድር አማራጮችን እንደሚያሰፋ ተናግረዋል።

ለአነስተኛ ኢንሹራንስ ሥራ ፈቃድ መስጠትና ምዝገባ መመሪያ አማካኝነት ከባንኮች በተጨማሪ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ለተንቀሳሽ ንብረት ዋስትና መስጠት እንደሚችሉና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትም ከባንኩ ፈቃድ አግኝተው ዋስትና መስጠት እንደሚችሉ ዶክተር ይናገር አብራርተዋል።

ብድሩ ሲሰጥ ዋስትና የሚያዝበት የተንቀሳቃሽ ንብረት ምዝገባ ማዕከላዊ በሆነ መልኩ እንደሚከናወንና የንብረት ተመን አወጣጥ ትመና ላይ ጥናት እየተደረገ ነው ብለዋል።

መመሪያዎቹን ለመተግበር የመረጃ ማደራጀትና የአደረጃጀት መዋቅር እንደሚዘረጋ አመልክተዋል።

ተንቀሳቃሽ ንብረትን በዋስትና ማስያዝ መመሪያ ላይ የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ መወሰዱንና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጊዜ ሂደት እንደሚፈቱም ገልጸዋል።

የመሠረተ ልማት አቅርቦትና ሌሎች የአሠራር ሥርዓቶች ሊኖሩ የሚችሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው መመሪያዎቹን ተግባራዊ ማድረግ አማራጭ እንደሌለው አመልክተዋል።

የፋይናንስ ተቋማቱ ለመመሪያዎቹ ተግባራዊነት ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ዶክተር ይናገር ጥሪ አቅርበዋል።

መመሪያዎቹ ከ2013 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በውይይቱ ላይ የባንኮች፣ የኢንሹራንስ ድርጅቶች፣ የሊዝ ኩባንያዎችና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችና እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም