በአዲሱ አመት አሁን ያጋጠሙትን አገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ አንድነትን ማጠናከር ይገባል...ፖለቲከኞች

149

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3/2012 (ኢዜአ) በአዲሱ አመት አሁን ያጋጠሙትን አገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ገለጹ።

ለአዲስ ዓመት የ'እንኳን አደረሳችሁ' መልዕክት ያስተላለፉት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እና የኢትዮ ጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አመራሮች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር በመግባባት መስራት ያስፈልጋል።

የአዴፓ ሊቀመንበር አቶ ትዕግስቱ አወሉ ''2012 ዓ.ም ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበትና ችግሮችን ለመፍታት ጥረት የተደረገበት ቢሆንም አዳዲስ ችግሮችም ተስተውለውበታል'' ብለዋል።

የለውጥ ጉዞው በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ጽንፍ በያዘ የዘረኝነት አስተሳብ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የሚፈጠሩ ጫናዎች የተነሳ አዝጋሚ ሊሆን መቻሉን ገልጸዋል።

ህግን ለማስከበር ጥፋተኛን በጥፋቱ ልክ የመጠየቅ ባህል መዳበር እንዳለበት አመልክተዋል።

በ2012 ከተስተዋሉ መልካም ተሞክሮዎች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትና የአገሪቱን የቱሪዝም ሃብት ለማልማትና ለማስዋብ እየተሰራ ያለውን ስራ በአብነት አንስተዋል።

የሚሰሩትን ስራዎች ለማስቀጠልና ፈተናዎችን ለማለፍ የውስጥ መግባባትን ማጠናከርና አገራዊ አንድነትን ማምጣት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

''መንግስት ህግ የማስከበሩን ሂደት አጠናክሮ መቀጠል አለበት'' ያሉት አቶ ትዕግስቱ፤ ሁሉም ወገን ከግጭት ውስጥ ወጥቶ የስራ ባህሉን ማዳበር ላይ ማተኮር እንደሚገባው ገልጸዋል።

የኢሶዴፓ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው አገሪቷ ከ2010 ጀምሮ የለውጥ ጉዞ ላይ መሆኗን አስታውሰው፤ ህዝብን በብሄርና በሃይማኖት በማነሳሳት ከፍተኛ ችግሮች እንደተፈጠሩ ገልጸዋል።

የታየው ችግር ህይወት እስከማጥፋትና ንብረት እስከማውደም የደረሰ መሆኑን የችግሩን ክብደት እንደሚያመላክት ተናግረዋል።

ለውጡ ከባድ ፈተና ያስተናገደ ቢሆንም ኢኮኖሚውን ጠብቆ ለማቆየት የተደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

''በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ ፕሮጀክቶች በፈተና ውስጥ የተከናወኑ ድንቅ ፕሮጀክቶች ናቸው'' ብለዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ የተገባደደው አመት ብዙ ተስፋ የታየበትና በርካታ ችግሮችም የተስተናገዱበት አመት እንደነበር ገልጸዋል።

አገሪቱን የተፈጥሮ አደጋ በተለይ ጎርፍ፣ የአንበጣ መንጋ፣ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝና መሰል ችግሮች ቢገጥሟትም አገራዊ እሴቶችን አስጠብቀን ማለፍ የተቻለበት እንደነበረ ተናግረዋል።

''በአገሪቱ ያለውን የባህል እና የሃይማኖት ልዩነት በማክበር አገርን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ በሚደረገው ጥረት አዲሱ ትውልድ ነገሮችን በተረጋጋና በሰከነ መንገድ አጢኖ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል'' ብለዋል።

''ቀጣዩ አመት፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የተስፋ በተለይ ወደ ዴሞክራሲ የምንሻገርበት አመት ይሁንልን'' ሲሉ ፓርቲዎቹ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም