ሴቶችን ከጥቃት መከላከል የሁሉም ዜጎች የቤት ሥራ መሆን ይገባዋል – ፌዴሬሽኑ

694

አዲስ አዲስ፣ ጳጉሜ 3/2012 (ኢዜአ) ሴቶችን ከጥቃት ለመከላከልና እኩልነታቸውን ማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች የቤት ሥራ መሆን እንደሚገባው የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ፌዴሬሽኑ ዛሬ ከተለያዩ የመዲናዋ ክፍሎች ከተውጣጡ ሴት ወጣቶች ጋር በመሆን የ2013 ዘመን ሴቶችን ከጥቃት በመታደግ ራዕያቸውን ልናግዝ ይገባል በሚል እሳቤ መድረክ አዘጋጅቷል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጥበቡ በቀለ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የሴቶች ጥቃትን ለማስቆም የጋራ ርብርብ  ማድረግ ያስፈልጋል።

”በተለይ የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ በርካታ ሴቶች፣ በቤተሰቦቻቸው ሳይቀር እየተደፈሩ ነው” ያለው ፕሬዚዳንቱ፣ይሄን ለማስቆም ዜጎች ሚናቸውን መጫወት አለባቸው ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ ጉዳዩ እልባት አንዲያገኝና ሴቶች ከሚያጋጥሟቸው ማህበራዊ ችግሮች ለማውጣት እንደሚሰራ አስታውቋል።

በመድረኩ  የጠንካራና አርዓያ ሴቶችን ተሞክሮ  ያካፈለው ወጣት ልዩነት ታምራት እንዳመለከተው  ”ሴቶች በብዙ ችግሮች መካከል አልፈው ለስኬት መድረስ ይችሉበታል።”

ነገር ግን ጾታዊ ጥቃቶች በሥነ ልቡናቸው ላይ በሚፈጥርቧቸው ተጽዕኖዎች በመታደግ ራዕያቸው እንዲያሳኩ ከጥቃቱ ልንጠብቃቸው ይገባል ብሏል።

በመድረኩ ከተሳተፉ ሴት ወጣቶች መካከል ወጣት ሐረግ ጌታሁን  በሰጠችው አስተያየት በአሁኑ ወቅት የሴቶች ጥቃት ለማስቀረት እየተደረገ ያለው ጥረት ”መልካም” ከሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል ትላለች።

”ነገር ግን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የራሳችንን ጉዳይ በዋናነት እኛው ራሳችን መፍታት  ስላለብን ወጣት ሴቶች በጉዳዩ ላይ በትኩረት ለመስራት  በ2013  እቅድ ይዘን  እየተንቀሳቀስን ነው” ስትልም ተናግራለች።