ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊያጋልጥ በማይችል መልኩ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስጀመር ጥናት ተደርጓል–ትምህርት ሚኒስቴር

817

 አዲስ አበባ  ጳግሜ  2/2012  (ኢዜአ) ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊያጋልጥ በማይችልና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ የመማር ማስተማር ሂደቱን በአዲሱ ዓመት ለማስጀመር ጥናት መደረጉን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። 

ሚኒስቴሩ እንዳለው በአንድ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን ቁጥር በመመጠንና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ትምህርት ማስጀመር በሚቻልበት መንገድ ላይ ጥናት ተደርጓል። 


የትምህርት ሚኒስተር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ የ2013 የትምህርት ዘመን የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን አመልክተዋል።

ኮሮናቫይረስ በፖለቲካ፣ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ዘርፍ በሳደረው ጫና ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጭ እንዲሆኑ መደረጉንም አስታውሰዋል።

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት ትምህርት መቋረጡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት አስተዋፅኦ ቢኖረውም በተማሪዎች በተለይም ከህጻናት እድገት አንጻር ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

በተለይ ህጻናት ትምህርት ዝግ ሆኖ ቤት በመዋላቸው ለአስገድዶ መደፈርና ያለዕድሜ ጋብቻ መዳረጋቸውን ሚኒስቴር ዴኤታው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ባሉ ከ42 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ከ700 ሺህ በላይ መምህራንና ከ26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ይገኛሉ።


“ወቅቱ ኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለበት በመሆኑ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ህብረተሰቡን እያነጋገረ ነው” ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ወረርሽኙ  የሚቆምበት ጊዜ ባለመታወቁ ትምህርት እንደሚጀመርና ይህም የጤና ጥበቃ የሚያስቀምጠውን መስፈርት ተግባራዊ በማድረግ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

ባለፈው የመማር ማስተማር ሂደት በአማካይ ከ60 እስከ 80 ተማሪዎች በአንድ ክፍል ውስጥ ይማሩ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር አቶ ሚሊዮን አስታውሰዋል።

በቀጣይ ትምህርት ሲከፈት በቅድመ መደበኛ 14 በመቶ የሚሆኑትን ትምህርት ቤቶች ከ20 እስከ 25 ተማሪዎችን ብቻ በአንድ ክፍል እንዲያስተምሩና አንድ ተማሪ በአንድ ዴስክ ብቻ እንዲቀመጥ ለማድረግ መታቀዱን አስረድተዋል።

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት ቀሪዎቹ 80 በመቶ ተማሪዎች በፈረቃ እንዲማሩና 6 በመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች ደግሞ ትምህርት ቤት በመገንባትና አማራጭ ማህበራዊ ተቋማትን በመጠቀም ለማስተማር ታቅዷል።

በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 24 በመቶ ወይም ከ20 እስከ 25 ተማሪዎች በአንድ ከፍል ውስጥ እንዲማሩ፣ 56 በመቶ በፈረቃ እንዲሁም 20 በመቶ ተጨማሪ ክፍል በመገንባት እንዲማሩ ተወስኗል።

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 19 በመቶ ተማሪዎች ወይም ከ20 እስከ 25 የሚሆኑት በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲማሩ እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በፈረቃ የሚማሩ ይሆናል።

ሌሎች 31 በመቶ ተጨማሪ ክፍሎችን በመገንባትና አማራጭ ማህበራዊ ተቋማትን በመጠቀም ለማስተማር መታቀዱንም አመልክተዋል።

በሽታን በመከላከል የትምህርት ተቋማትን ስራ ለማስጀመር ተቋማቱን ማስፋት እንደሚገባም አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል።

ኦሮሚያ ክልል ሃብት በማሰባሰብ 30 ሺህ አዳዲስ ክፍሎችን መገንባቱን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣  “አማራ ክልልም በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የክፍል እጥረት ችግር ለመቅረፍ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው” ብለዋል።

ተማሪዎች በተረጋጋ ሁኔታ እንዲማሩ የቀደመው የመማር ማስተማር ስልት በአዲስ መልክ እንደሚሆን ጠቁመው፣ ይህም የቡድን ስራን ጨምሮ የተማሪዎችን አካላዊ ንክኪን ሊያስቀር በሚችል መልኩ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት የትምህርት ቤቶች አከፋፈት ጥናቱን መሰረት ያደረገ ይሆናል።

ትምህርት ቤቶች በተመሳሳይ ወቀት አንድ ላይ ሊከፈቱ እንደማይችሉና ደረጃ በደረጃ የመክፈት ሂደት እንደሚኖር ገልጸው፣ አጀማመሩ ከክልል ክልልና ከዞን ዞን ሊለያይ እንደሚችል አመልክተዋል።

ይህንን ተከትሎ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ጭማሪ እየጠየቁ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን በሚያደርጉ ተቋማት ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶችን እስከመዝጋት የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አመልክተዋል።