በደሴ ከተማ በኢንተርፕራይዞች ለውጭ ገበያ ከቀረቡ ምርቶች ከ68 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

61
ደሴ ሐምሌ 6/2010 በደሴ ከተማ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች ዘንድሮ ለውጭ ገበያ ካቀረቧቸው ምርቶች ከ68 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የከተማዋ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡ መምሪያው ከአነስተኛ ታዳጊ ወደ ታዳጊ መካከለኛ ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራዞች እውቅና ሰጥቷል። የመምሪያው ኃላፊ አቶ መከተ ዘውዱ እውቅና ለመስጠት በተዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ እንዳሉት ገቢው የተገኘው በ2010 በጀት ዓመት በከተማዋ የሚገኙ አስር ኢንተርፕራይዞች ለውጭ ገበያ ካቀረቧቸው ምርቶች ነው። በኢንተርፕራይዞቹ ተመርተው ለገበያ ከቀረቡት መካከል ፈሳሽ ሳሙና፣ የባህል አልባሳት፣ አልጋ ልብሶች፣ የእጅ ሥራዎች፣ የባልትና ውጤቶችና መሰል ምርቶች ይገኙበታል፡፡ ምርቶቹ ለአሜሪካ፣ ቱርክ፣ ጅቡቲና መካከለኛው ምስራቅ የተላኩ ሲሆን በዚህ ኢንተርፕራይዞቹ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለውጭ ገበያም ማምረት እንደሚችሉ ትምህርት ያገኙበትና ዓለም አቀፍ የገበያ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል። ወደ መካከለኛ ባለሃብት የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብትና የፈጠራ ብቃታቸውን በማቀናጀት የተሻለ ሥራ እንዲሰሩም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አቶ መላኩ እንዳሉት ወደ ታዳጊ መካከለኛ የደረጃ ሽግግር የተደረገላቸው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 10 ኢንተርፕራይዞች ሲሆኑ እስከዛሬም ከ300 ለሚበልጡ ሰዎች የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ ኢንተርፕራይዞቹም በእንጨትና ብረታ ብረት፣ በባልትና ውጤቶች፣ በወተት ላም እርባታ፣ በዶሮ እርባታ፣ በጋራዥና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች የተሰማሩ ናቸው፡፡ በ2007ዓ.ም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ሕክምና ተመርቆ ከአንድ ጓደኛው ጋር በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማራው ዶክተር ነጋ ቢያዝን በበኩሉ ባለፉት ዓመታት ስኬታማ ስራዎችን እንዳከናወኑ ተናግሯል። "በአሁኑ ወቅት ወደ መካከለኛ ባለሃብትነት መሸጋገራችን በላቀ የኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት፣ በአነስተኛ ዋጋ የግንባታ ቦታዎችን ለማግኘትና የብድር ተጠቃሚ ለመሆን ያግዘናል ሲል" ገልጿል። ይህም ለተሻለ አፈጻጸም እንደሚያነሳሳው ነው ያስታወቀው። ሽግግሩ ስኬታማ እንዲሆን ላለፉት አምስት ዓመታት በጉልህ የተስተዋለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ ብድር ለማግኘት ያለው ቢሮክራሲና ውጣ ውረድ፣ እንዲሁም የቦታ አቅርቦት ችግር ሊፈታ እንደሚገባ ነው ዶክተር ነጋ የገለጸው። በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ ይሄን ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት ነው የጠየቀው፡፡ የሆጤ ክፍለ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንደሰን ሽመልስ" ከተማ አስተዳደሩ የደረጃ ሽግግር ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የደረሱበትን ደረጃ መከታተል ይኖርበታል" ብለዋል። የሚያጋጥማቸው ችግር በሂደት የሚፈታበትን መንገድ ቀርቦ የማመላከት ኃላፊነት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት። እንደ ኃላፊው ገለጻ ባለፉት ዓመታት ለበርካታ ኢንተርፕራዞች የደረጃ ሽግግር ቢደረግም ኢንተርፕራዞቹ በብድርና በቦታ አቅርቦት እጥረት የሚጠበቅባቸውን ያህል ሳይንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡ የከተማዋ ብአዴን ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደመቀ ቦሩ በበኩላቸው ስራ እጥነትን ለመቅረፍም ሆነ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ደረጃ ለማሻሻል ኢንተርፕራይዞች የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል። ኢንተርፕራይዞቹ ያሉባቸው ችግሮች ያለምንም ውጣ ውረድ ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ በደሴ ከተማ 8 ሺህ 181 አባላት ያሏቸው 4ሺህ 157 ኢንተርፕራይዞች እንዳሉ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም