የተገነቡ የውሃ ተቋማት ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫና አስቀርተዋል…የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ነዋሪዎች

61

 አዲስ አበባ  ጳግሜ  2/2012  (ኢዜአ) በዞኑ የተገነቡና በጸሐይ ኃይል በሚደገፉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ30 ሺህ በላይ የገጠር ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ውሃ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።

“በምዕራብ በለሳ ወረዳ የቃላይ ቀበሌ ነዋሪ ሴት አርሶ አደር ጥገት ታከለ ንጹህ መጠጥ ውሃ ለማግኘት ለወላድ ሴቶች ፈታኝ ነበር” ብለዋል።

በተለይም ህጻናትን ለያዙ እናቶች ደግሞ ውሃ ቀድቶ ለመመለስ ችግሩ የበረታ እንደነበርም የገለጹት አርሶ አደሯ “አሁን ደጃፋችን ላይ ንጹህ መጠጥ ውሃ በመገንባቱ የሴቶች እንግልት ተወግዷል ከውሃ ወለድ በሽታም ነጻ ሆነን እፎይታ አግኝተናል” ብለዋል።

“ውሃ ፍለጋ የአንድ ሰአት የእግር ጉዞን ጨምሮ ውሃ ለመቅዳትም ከሁለት እስከ ሶስት ሰአት የሚፈጅ ወረፋ ጠብቀን ወደ ቤታችን ለመመለስ እንገደድ ነበር” ያሉት ደግሞ በወረዳው የቃላይ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እትዬ ዳምጤ ናቸው፡፡

“ዛሬ በአቅራቢያችን በተገነባልን የውሃ ተቋም ችግራችን በመወገዱ እንደልባችን ንጹህ ውሃ ቀድተን ለመጠጣት በመብቃታችን መንግስትን እያመሰገን ነው” ብለዋል፡፡ 

በዞኑ ውሃ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ ተወካይ ሃላፊ አቶ ዮሴፍ አረጋዊ እንደተናገሩት በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት አመት የተገነቡት በጸሐይ ኃይል የሚሰሩት 22 የውሃ ተቋማት 50 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ናቸው።

ተቋማቱ የተገነቡት በምእራብና ምስራቅ በለሳ፤ በምስራቅና ምእራብ ደንቢያ እንዲሁም በጭልጋና በጎንደር ዙሪያ ወረዳዎች ውሰጥ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች መሆኑንም ተናግረዋል።

“በመንግሰት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና በህብረተሰቡ የጉልበት ተሳትፎ ጭምር የተገነቡት የውሃ ተቋማት የገጠሩ ህብረተሰብ ከዚህ ቀደም ውሃ ፍለጋ ረዥም ርቀት በመጓዝ ይደርሰበት የነበረውን እንግልት ያስቀሩ ናቸው” ብለዋል።

“ቴክኖሎጂው በተለይም አለምን እየፈተነ ካለው የአየር ንብረት ለውጥ አኳያ በታዳሽ ሃይል የሚሰራ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው” ያሉት አቶ ዮሴፍ በነዳጅ የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮችን የነዳጅ ወጪ በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ እንደሆነም ተናግረዋል።

የውሃ ተቋማቱ መለስተኛና ጥልቅ ጉድጓድ በመቆፈር የተዘጋጁና እያንዳንዳቸው በአንድ ጊዜ አራት ሰዎችን የሚያስተናግዱ የውሃ ቦኖዎች የተገነቡላቸው እንደሆም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ተቋማቱ 27ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝ አቅም ያላቸው ''ፓዮራን'' የተባሉ ዘመናዊ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችና በጸሐይ ሃይል የሚሰሩ የውሃ ፓንፖች የተገጠመላቸው እንደሆኑም ጠቁመዋል።

 የምዕራብ በለሳ ወረዳ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መርቆ አስታጥቄ  በበኩላቸው በወረዳው በሶላር ኃይል የሚሰሩ አምስት የውሃ ተቋማት ተገንብተው 6ሺህ ያህል ነዋሪዎች የንጽህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህም ቀደም ሲል ህብረተሰቡ ለንጽህ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ  ያባክነው የነበረው ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ለሌላ ልማት ለማዋል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።


በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት አመት በ19 ሚሊዮን ብር ወጪ 420 የእጅ ጉድዶችና ምንጮች ተቆፍረውና ጎልብተው ከ95ሺ በላይ የህብረሰብ ክፍሎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም