ችሎቱ ዐቃቤ ህግ በእነ አቶ ጃዋር ላይ በጠየቀው የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

242

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 29/2012(ኢዜአ) ዐቃቤ ህግ በወንጀል በተጠረጠሩት በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ በጠየቀው የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ትዕዛዝ ለመስጠት ለጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ተረኛ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ተረኛ ችሎት አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ቀርበዋል።

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ላይ በመዝገብ ቁጥር 215585 የቀዳሚ ምርመራ 15 ምስክሮችን ለማሰማት ጠይቆ የነበረው ዐቃቤ ህግ 10 ምስክሮችን አሰምቷል።

ዐቃቤ ህግ ቀሪዎቹን ምስክሮች በተለያየ ምክንያት አሁን ማሰማት እንደማይፈልግ ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል።

ምስክር መስማቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ የቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ግልባጭ በደረሰው በ15 ቀናት ውስጥ ክስ ለመመስረት ጊዜ እንዲሰጠው ችሎቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው የተጠየቀው የክስ መመስረቻ ጊዜ ረጅም መሆኑን በመግለጽ የተቃውሞ አቤቱታ አቅርበዋል።

ተጠርጣሪ ደንበኞቻቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበርም ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ የተጠርጣሪ ጠበቆች ባቀረቡት አቤቱታ ላይ በሰጠው ምላሽ ያሉትን ማስረጃዎች ሙሉ ለሙሉ አለማቅረቡንና የሚያቀርባቸው ሌሎች ማስረጃዎች እንዳሉት ለችሎቱ ገልጿል።

“የቀዳሚ ምርመራ ምስክር የምናሰማው ካሉን ምስክሮች ውስጥ ሊጠፉ የሚችሉትን ነው” ብሏል ዐቃቤ ህግ።

የተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት የሰው ህይወት የጠፋበትና ተጠርጣሪዎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስፈርድ በመሆኑ የዋስትና መብት የሚያስከለክል እንደሆነ በመግለጽ የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ዐቃቤ ህግ ጠይቋል።

ግራና ቀኙን የተመለከተው ችሎቱ ዐቃቤ ህግ በጠየቀው የ15 ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዐቃቤ ህግ ዛሬ ያሰማውን የአንድ ምስክር ቃል ገልብጦ ከመዝገብ ጋር እንዲያያዝ አዟል።