ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራዎች ስኬታማነት ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን

189

ድሬዳዋ/ አዳማ/ ሀዋሳ/ አርባምንጭ ፤ ሚያዚያ 20 /2016(ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራዎች ስኬታማነት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

ኮሚሽኑ እስካሁን ባለው ሂደት መሠረታዊና የህዝብ ተሳትፎ ባማከለ የተሳታፊዎች ልየታና መረጣ በ10 ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች እንዳገባደደ ቀደም ብሎ ተገልጿል።

የተሳታፊዎች መረጣ በተካሄደባቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ሰሞኑን አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር እንደሚጀመር ተመልክቷል።

ኮሚሽኑ ቅድመ ዝግጅቶች ሲያደርግባቸው ከቆዩት ከተሞች መካካል አሶሳ፣ ድሬዳዋ ፣ አዳማ ፣ ሀዋሳና ወላይታ ሶዶ ከተሞች ይገኙበታል።

በእነዚህ ከተሞች በኮሚሽኑ የስራ ሂደቶች ላይ ተሳትፎ የነበራቸውና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት፤ የምክክር ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት  ከታች ጀምሮ ተሳታፊዎች እየለየ መምጣቱ አሳታፊነቱንና ተአማኒነቱን የሚያሳይ መሆኑን ተገንዝበዋል።

የድሬዳዋ ነዋሪ አቶ ደረጀ ጉተማ ፤ ኮሚሽኑ በመላው አገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መሰራታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር እየሰራ እንደሚገኝ ግንዛቤ እንዳላቸው አመልክተዋል።

የምክክር ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የበለፀገች አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል እያመቻቸ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል። 

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ተልዕኮ ስኬታማ እንዲሆን የድርሻቸው እንደሚወጡ አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

ለኮሚሽኑ ተልዕኮ መሳካት ዜጎች በሙሉ የድርሻችንን ኃላፊነት መወጣት ይገባናል ብለዋል።

የአዳማ ከተማ የአገር ሽማግሌዎች ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ፈይሳ መገርሳ በበኩላቸው፤  በኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜ በተዘጋጁ መድረኮች ላይ በመሳተፍ የምክክሩ ዓላማ ላይ በቂ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በምክክር ሂደቱ ሁሉም የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉት አካላት መሳተፍ አለባቸው ያሉት አቶ ፈይሳ፤  ከሴቶች፣ ወጣቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ከተወከሉት አካላት ጋር  መድረኮች ላይ በመሳተፍ ሀሳቦችንና ግብዓቶችን ማከላቸውን አውስተዋል።

ለምክክር ኮሚሽኑ ስራ መሳካት አስፈላጊው ድጋፍ ማድረጋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በሚኖሩበት ሃዋሳና የሲዳማ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችም የተጣላን በማስታረቅና በማስማማት የሽምግልና ሃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ  የነዋሪ የሆኑት የሲዳማ ክልል የአገር ሽማግሌ መጋቢ ጢሞቲዎስ በራሳ ናቸው።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለአገሪቱ ሰላምናአንድነት መጠበቅ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው  አመልክተው፤ የቆዩ ችግሮቻችን በመነጋገርና በመመካከር የሚፈቱ ናቸው ብለዋል።

 ለዚህም  ከሚሽኑ  እያመቻቸ ያለው ተግባር አበረታችና የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ለምክክር ኮሚሽኑ ውጤታማነት እያንዳንዱ ዜጋ  ለአገርና ለህዝብ አንድነት የሚያግዙ ሃሳቦች ማመንጨት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ 

ለዚህም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸው፤ ሲንከባለል የመጣው የኢትዮጵያ ችግር መቋጫ የሚያገኘው በአገራዊ ምክክር ነው ብለዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ  ነዋሪ  ወይዘሮ ብሩክ ባልቻ ፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከታች ጀምሮ ተሳታፊዎች እየለየ መምጣቱ አሳታፊነቱንና ተአማኒነቱን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

መወያየት ለሁሉ ችግር መፍትሄ መሆኑን አመልክተው፤  በዚህም ባሳለፍናቸው ጊዜያት የተፈጠሩ ችግሮች እልባት ለመስጠት ዕድሉን መጠቀም ይገባናል ሲሉም ተናግረዋል።

አሁን ላይ አገራችን በልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች ያሉት ወይዘሮ ብሩክ ፤ ይህን በዘላቂ ሰላም  ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑንና ለኮሚሽኑ ስራ መሳካት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ይህ ስራ ከግብ እንዲደርስ ሀሳብ ከመስጠት ጀምሮ ሁሉም ዜጋ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበትም አመልክተዋል

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም