ከተማን ውብና ፅዱ በማድረግ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

149

ሠመራ፤ ሚያዚያ 20 /2016(ኢዜአ)፦  ከተማን ውብና ፅዱ በማድረግ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ ተናገሩ።

እንደ አገር የተጀመረው የአካባቢ ጽዳትና ውበት ዘመቻ በአፋር ክልል ደረጃ ባለፈው ሳምንት መጀመሩን ተከትሎ የከተማ አስተዳድሮችና ወረዳዎችም ዘመቻውን እየተገበሩት ይገኛሉ።

"ብክለት ይብቃ-ሁሉም ይንቃ" በሚል መሪ ሐሳብ  እየተካሄደ ያለው  የአካባቢ ብክለትን የማስወገድ ንቅናቄ መድረክ በክልሉ እስከ መስከረም 30 ቀን 2017ዓ.ም የሚቆይ እንደሆነም ተገልጿል።

ዘመቻውን በሠመራ ሎጊያ ከተማ ያስጀመሩት ከንቲባ አብዱ ይህን  የንቅናቄ ዘመቻ በተከታታይነት የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የመንግስት ተቋማት ሆቴሎችና የግል ተቋማት በጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች መሆናቸውን የገለፁት ከንቲባው፤ ከተማችንን ውብ፣ ፅዱ እና ለነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ሥፍራ የመፍጠሩ ስራ ዘላቂና የዘወትር ትኩረታችን ነው ብለዋል።

በዚሁ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጂነር ገቡ መሐመድ በበኩላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን መርሃ ግብር ማከናወን መጀመራቸውን ገልፀዋል።

ምክትል ሃላፊው አክለውም ስራዎቻችንን በብቃት ልንፈፅም የምንችለው ከብክለት ፅዱ የሆነ አካባቢ መፍጠር ሲቻል ነው ብለዋል።

በጽዳት ሥራው ተሳታፊ ከሆኑት የሠመራ  ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አምቢያ አብዱ በበኩላቸው የከተማችንን ውበት ንፁህ በማድረግ እንግዶች ወደ አካባቢያችን በመጡ ጊዜ የሚረኩበት እና በጥሩ የሚመለከቱት መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

ሰለሆነም ለከተማዋ መደረግ ያለበትን ህብረተሰብን ከማስተባበር ጨምሮ ፅዱ እና ከብክለት ነፃ የማድረግ ስራ  ላይ በግንባር ቀደምትነት እሳተፋለሁ ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም