ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ተመርቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው- የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ

76

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20/2016(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ተመርቶ ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ መሆኑን አስታወቀ።

ኢንተርፕራይዙ ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑና በሽታን መቋቋም የሚችሉ ከ20 በላይ የሰብል ዓይነቶች ምርጥ ዘር እያመረተ መሆኑን ገልጿል።

የኢንተርፕራይዙ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ጫላ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት ኢንተርፕራይዙ በክልሉ ከ80 በመቶ በላይ እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ ከ60 በመቶ በላይ ምርጥ ዘር ያቀርባል።

ኢንተርፕራይዙ በኩታ ገጠም በተደራጁት አርሶ አደሮች፣ ባለሀብቶችና በራሱ የዘር ብዜት እርሻዎች በዚህ ዓመት ከ500 ሺህ በላይ ኩንታል የተመረተ ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 300 ሺህ ኩንታል ንጹህ ምርጥ ዘር ለስርጭት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

እስካሁንም ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል።

ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከሚያስችሉ ውስጥ ምርጥ ዘር በስፋት ለአርሶ አደሩ እንዲደርስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ኢንተርፕራይዙ በራሱ በሚያለማቸው በባሌ፣አርሲ እና በምዕራብ ወለጋ በሚገኙ 13 እርሻዎች ላይ እንደ አካባቢው ስርዓተ ምህዳር ተስማሚነት ምርጥ ዘር እየተባዛ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምርታማነታቸው ከፍተኛ የሆኑና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ጤፍን ጨምሮ ከ20 በላይ የሰብል ዓይነት ምርጥ ዘሮችን በማባዛት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም