የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል

194

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 20 /2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ዋንጫ ሁለተኛ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ዛሬ ይካሄዳል::

የኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ዛሬ ይደረጋል።

የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።

ሀዋሳ ከተማ በሩብ ፍጻሜው አርባ ምንጭ ከተማን 2 ለ 0 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከነማን 4 ለ 1 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸው ይታወቃል።


 

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ቤንች ማጂ ቡና እና መቻልን አሸንፏል።

ክለቡ በኢትዮጵያ ዋንጫ እስከ አሁን ባደረጋቸው 3 ጨዋታዎች 7 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ 1 ጎል አስተናግዷል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በዚህ ውድድር አስቀድሞ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ወልዲያ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማን ማሸነፉ ይታወቃል።


 

በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚመሩት ቡናማዎቹ በውድድሩ ባደረጓቸው 3 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ሲያስቆጥሩ የተቆጠረባቸው 1 ግብ ብቻ ነው።

የሁለቱ ክለቦች አሸናፊ ከወላይታ ድቻ  በፍጻሜው የሚገናኝ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ዋንጫ ትናንት በተደረገው የመጀመሪያ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያ መድንን 1 ለ 0 በማሸነፍ ለፍጻሜ ማለፉ ይታወቃል።


 

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ በቀጣዩ ዓመት በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም