ስታርት አፖችን በተደራጀ  አግባብ ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ-- ሙፍሪያት ካሚል 

83

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦  ስታርት አፖችን በተደራጀ  አግባብ ለመደገፍ እየተከናወኑ ያሉ  ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር  ሙፍሪያት ከሚል ገለጹ።

ለሦስት ሳምንታት በሳይንስ ሙዚየም ሲካሄድ የቆየው የስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ ተጠናቋል፡፡

በማጠቃለያ መርሃ -ግብሩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ እና ሌሎችም የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

በአውደ ርዕዩ  አዳዲስ በቴክኖሎጂ የታገዙ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው ወጣቶች ተሞክሯቸውን በስፋት ለሌሎች ያጋሩበት ፣ጀማሪ ስታርት አፖችን በማስተዋወቅ የተሻለ የፈጠራ ስራዎች እንዲዳብሩ ለማስቻል ምቹ ምህዳር የተፈጠረበት መርሃ ግብር እንደነበር በመድረኩ ተገልጿል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ መንግስት ለስታርት አፖች  ምቹ ምህዳር ለመፍጠር ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ለአብነትም ዘጠኝ  የሚደርሱ የአሰራር ማሻሻያ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፤ ማሻሻያዎቹ የፋይናስ አቅርቦትን ጨምሮ ለስታርት አፖች የተቀላጠፈ አሰራርን ገቢራዊ የሚያደርጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ለተደረጉ ማሻሻዎች ተግባራዊነት ቀጣይነት ያለው ክትትል እንደሚደረግም ነው ያነሱት፡፡

አውደ ርእይ ከማዘጋጀት ባሻገር ስታርት አፖችን በተደራጀ አግባብ ለመደገፍ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም እንዲሁ፡፡

             ​​​
           
 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ (ዶ/ር) ባይሳ በዳዳ በበኩላቸው፤ አውደ ርእዩ በተለይ ጀማሪ ስታርት አፖች ሃሳባቸውን ለማስተዋወቅ እድል ያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት እንደ ሀገር 50 ስታርታፖች ብቻ የነበሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው  በአሁኑ ወቅት ከ900 በላይ ስታርት አፖች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

በአውደ ርዕይው ስራዎቻቸውን ለውድድር ያቀረቡ እና ከአንድ እስከ ሦስት የወጡ ስታርት አፖችን እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በአውደ ርዕዩ  300 የሚደርሱ ስታርት አፖች ለእይታ የበቁበት፤ የተለያዩ ትልልቅ የውይይት መድረኮች የተካሄዱበት፤ ዘጠኝ  የሚደርሱ የፖሊሲ የሪፎርም አቅጣጫዎች የተቀመጡበት  መሆኑ ተገልጿል።

በአውደ ርእዩ  በግብርና ፣ጤና፣ በኢንዳስትሪ፣በኢነርጂና ሌሎችም ዘርፎች ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሃሳቦችና ምርቶች ለእይታ የበቁበት  ሲሆን ይህም ውጤታማ የስራ ፈጣሪነትን ለመተግበር ምቹ ምህዳር የፈጠረ መሆኑን ተገልጿል።

በአውደ ርዕይው የተሳተፉ የስታርት አፕ ስራዎችን  ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም