ስራ ከድህነት የምንወጣበትና የአሸናፊነት ታሪካችንን በደማቁ የምናጽፍበት መሳሪያችን ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

166

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ ስራ ከድህነት የምንወጣበትና ደማቁን የአሸናፊነት ታሪካችንን በደማቁ የምናጽፍበት መሳሪያችን ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ሰላም ቁልፉ መንገድ ነው ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል። 

በአጭር ጊዜ ወደ ስራ የተመለሰው የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክም ሆነ ሌሎች የክልሉ የልማት ስራዎችን ለማጠናከር ሰላም ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

በህልውና ጦርነቱ የኢንዱስትሪ መንደሮቿን ጨምሮ የከፋ ጉዳት የደረሰባት የኮምቦልቻ ከተማ በተገኘው ሰላም ወደ ቀደመ ድምቀቷ መመለሷን ዛሬ ተመልክተናል ሲሉም ገልጸዋል። 

በኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ የጎበኘናቸው አምራች ድርጅቶች ከክልሉ አልፎ ለሀገር እድገት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያላቸውን ምርቶች በሙሉ አቅም እና ጥራት እያመረቱ እንደሆነ አይተናል ብለዋል።


 

ምርቶቹ በከፍተኛ ጥራት ተመርተው ወደ ውጭ የሚላኩ ናቸው ያሉት አቶ ተመስገን በቀጣይ የሀገር ውስጥ ገበያውን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ 

መንግስትም ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
  
በሌላ በኩል ጥያቄዎችን ከሰላም ውጭ በመሳሪያ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀስ ሃይል ወደ ውይይትና ምክክር እንዲመለስ ከፌዴራል መንግስትም ሆነ ከክልሉ የቀረበውን ጥሪ እንዲጠቀም በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ ብለዋል።

ከሰላም እና ከውይይት ውጭ በጠመንጃ ጥያቄን ለማስመለስ የሚደረግ ሙከራ የክልሉን ልማት ወደ ኋላ የሚመልስ፣ የማይሳካና አክሳሪ በመሆኑ ይህን ለማስቆም የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግስት ህግና ስርዓትን ለማስከበር የጀመረውን ስራ ይቀጥላል ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም