በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ዲጂታል የመማር ማስተማር ስራን የሚያሳልጥ ስቱዲዮ ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ

103

ድሬዳዋ፤ ሚያዚያ 19/2016(ኢዜአ)፦ በምስራቅ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ዲጂታል የመማር ማስተማር ሥራን ለማሳለጥ የሚያስችልና በ25 ሚሊዮን ብር የተገነባ ዲጂታል ስቱዲዮ ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የተገነባውን ዲጂታል ስቱዲዮውን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደምና ዲጂታል የመማር ማስተማር ሥራውን እየደገፉ ያሉት የአጋር ተቋማት አመራር አባላት ናቸው።

በምረቃው ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዲጂታል የመማር ማስተማር ሥራን ለመጀመርና ስኬታማ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።

በዩኒቨርሲቲውም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በ25 ሚሊዮን ብር ዲጂታል ስቱዲዮ እንደተገነባ ገልጸዋል።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተከናወኑ የሚገኙ ዲጂታል የመማር ማስተማር ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ ማሳካት ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግም ያግዛል ሲሉ ገልጸዋል።

ዶክተር ኡባህ እንዳሉት፤ በዩኒቨርሲቲው ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት በጀመረው ዲጂታል ስቱዲዮ የሚጠቀሙት በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ያሉት የድሬዳዋ፣ የሐረማያ፣ የኦዳቡልቱም፣ የጅግጅጋ እና የቀብሪደሃር ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

በዩኒቨርሲቲው እስካሁን ሁለት የትምህርት ዓይነቶችን በሙከራ ደረጃ በ"ኦን ላይን" ማስተማር እንደተጀመረ የገለጹት ዶክተር ኡባህ፣ ለመምህራን በተለያዩ የዲጂታል ትምህርት ቀረፃዎች ላይ ስልጠና ተሰጥቶ ለመማሪያ የሚሆኑ ማንዋሎች ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ዲጂታል የመማር ማስተማር መርሃ ግብርን ዕውን ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት የሚመሩት በትምህርት ሚኒስቴር መሆኑም ተመላክቷል።

የዩኒቨርሲቲው የዘርፉ አመራር አባላት ዲጂታል የመማር ማስተማር ሥራውን በተሟላ መንገድ ማስጀመር በሚቻልበት መንገድ ላይ ዛሬ መክረዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም