በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ለማድረስ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

86

ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መጠናከር ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።

የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የአማራ ክልል ግብርና ሜካናይዜሽን ፎረም በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው በወቅቱ እንዳሉት፣ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ሜካናይዜሽንን አስፋፍቶ መጠቀም ተገቢ ነው።

በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን አቅርቦት እየተሻሻለ ቢሆንም፤ በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ኋላ ቀር የእርሻ መሳሪያዎችን በመጠቀም በሚፈለገው ልክ የሰብል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደማይቻል ጠቁመዋል።

ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በጥራት መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ፎረሙ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በጋራ ተወያይቶ በመፍታት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ከሚታረሰው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 42 በመቶ የሚሆነው ለግብርና ሜካናይዜሽን እርሻ የተመቸ ቢሆንም እስካሁን ማረስ የተቻለው 14 በመቶ ብቻ ነው።

መንግስት ለድርጅቶች ብድር አመቻችቶ የእርሻ ትራክተሮችና ኮምባይነሮችን ወደ ክልሉ እንዲያስገቡ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም የክልሉን የግብርና እንቅስቃሴ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።


 

የቲዜድ ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ካምፓኒ ዋና ሥራ አስኪያጅና የክልሎች ግብርና ሜካናይዜሽን ፎረም አስተባባሪ አቶ ቴዎድሮስ ዘውዱ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በሲዳማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ፎረሞች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

ፎረሞቹ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ወሳኝ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሚስተዋሉ የሰለጠነ የሰው ሀይል፣ የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ የፋይናንስና መሰል ችግሮችን ለማቃለል ያግዛሉ ብለዋል።


 

ድርጅቱ ከማጭድ ጀምሮ እስከ ትራክተር በማቅረብ የድርሻውን እየተወጣ ነው ያሉት ደግሞ የአምባሰል ንግድ ሥራዎች ድርጅት የክልሉና የእህት ኩባንያ አቅርቦት ቡድን መሪ ወይዘሮ ፀሐይ ተስፋዬ ናቸው።

ድርጅቱ እስካሁን ድረስ ከ220 በላይ የእርሻ ትራክተሮችን አስገብቶ ማሰራጨቱን ጠቅሰው፤ ከ30 በላይ ኮምባይነሮችም ወደ ክልሉ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።

በመድረኩ ላይ ከክልሉ ግብርና ቢሮ፣ ከምርምር ማዕከላት፣ ከህብረት ሥራ ማህበራት፣ ከቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅቶች፣ ከባንኮች፣ ከዩኒየኖች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም