በአዲስ አበባ ኢንዱስትሪዎች የሚገጥሟቸውን የአሰራር ማነቆዎች በመቅረፍ  የማምረት አቅማቸውን  ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

93

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ  የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚገጥሟቸውን የአሰራር ማነቆዎች በመቅረፍ  የማምረት አቅማቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ሲካሔድ የቆየው ከተማ አቀፍ "የኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት" ንቅናቄ በዛሬው እለት ተጠናቋል፡፡

በማጠናቀቂያ መርሃ ግብሩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በመዲናዋ በርካታ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በስራ እድል ፈጠራ፣ በውጭ ምንዛሬ ግኝት እና በኤክስፖርት ዘርፍ ጉልህ ሚና እያበረከቱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለአንድ አገር ኢኮኖሚ ሽግግር ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት ከንቲባዋ፤ ከዚህ አኳያ በአዲስ አበባ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ በተለይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ እድገት ያለውን ድርሻ ለማሳደግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪው የሚገጥመውን የአሰራር ማነቆ መፍታት ደግሞ ትኩረት ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ባለፉት ሶስት ዓመታት 162 የመስሪያ ቦታዎች ለኢንዱስትሪዎች እንዲሰጡ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በውሃ፣ መብራት፣ መንገድና መሰል መሰረተ ልማቶች ላይ ይገጥማቸው የነበረውን ችግር ለማቃለል በተሰራ ስራ ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመላክተዋል፡፡ 

ከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪዎችን አቅም ለማሳደግ የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም መጀመሩን የጠቆሙት ከንተባዋ፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ተመርተው ወደ ውጪ ከተላኩ የተለያዩ ምርቶች ከ667 ሚሊዮን ዶላር  በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉንም እንዲሁ፡፡

በመርሃ ግብሩ የተሻለ ካፒታል በማስመዝገብ የደረጃ ሽግግር ላደረጉ ኢንዱስትሪዎች እውቅና ተሰጥቷል፡፡

የደረጃ ሽግግር ካደረጉት መካከል ወጣት እየሩስዓለም መለሰ እና ወጣት ናስር የኑስ መንግስት ባመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታና የብድር አቅርቦት ለደረጃ ሽግግር መብቃታቸውን ገልጸዋል፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም