የብዝኃ ማንነት ባህላዊ ኃብቶቻችንን በመጠበቅ በሕዝቦች መካከል ትስስርና የወል ትርክት ለመገንባት እየተሰራ ነው- አቶ ቀጀላ መርዳሳ

84

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 19/2016(ኢዜአ)፦ያሉንን የብዝኃ ማንነት ኃብቶችን በመጠበቅ በሕዝቦች መካከል ትስስርና የወል ትርክትን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

የፊቼ ጫምባላላ በዓል የማጠቃለያ መርሃ-ግብር  በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ፊቼ ጫምባላላ ለሀገር ግንባታና ለማኅበረሰብ ትስስር ሚናው የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡


 

የብዝኃ ማንነት ባህላዊ ኃብቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ በሕዝቦች መካከል ትስስርንና የወል ትርክቶችን  ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከዚህ አኳያ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህላዊ እሴቶች ለማልማት በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡ 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዘመናት ቅብብሎሽ ዛሬ ላይ የደረሰው የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ ከሲዳማ ሕዝብ አልፎ የሀገርና የዓለም ኃብት እንዲሆን ከፍተኛ ሥራ መከናወኑን  ገልፀዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲዳማ ባህል ማዕከል የሚገነባበት ቦታ በመስጠትም  አዲስ አበባ የሁሉም ቤት መሆኗን በተግባር ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ይህን የዓለም ቅርስ የሆነ አኩሪ በዓል በመጠበቅ ትውልዱ በአግባቡ እንዲረዳው ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።  


 

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር፤ አዲስ አበባ ብዝኃነትን በማስተናገድ ፈጣን ልማትን በማረጋገጥ ለኑሮና ለሥራ የምትመች ከተማ መሆኗን በተግባር እያረጋገጠች ነው ብለዋል፡፡

ፍቼ ጫምባላላ የአብሮነት በዓል በመሆኑ ለሕብረ-ብሔራዊ እህትማማችነትና ወንድማማችነት እንዲሁም ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለማዋል ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል። 


 

ፊቼ ጫምባላላ እና መሰል ባህላዊ ፌስቲቫሎችን በቱሪዝም መስህብነት በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ በማዋል ተወዳዳሪ የቱሪዝም መዳረሻዎች በመፍጠር ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ደግሞ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ናቸው።

የቱሪዝም ሚኒስቴርም ፊቼ ጫምባላላን ጨምሮ የሲዳማ ክልል የቱሪዝም ኃብቶች እንዲጠበቁ፣ እንዲለሙና እንዲተዋወቁ ለማድረግ ከክልሉ መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡         

በበዓሉ ላይ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሲዳማ ክልልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የሲዳማ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ፊቼ ጫምባላላ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከማይዳሰሱ ቅርሶች ምድብ የሰው ልጆች ወካይ ቅርስ ሆኖ ኅዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም የዓለም ኃብት ሆኖ ተመዝግቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም