37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

147

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 18/2016(ኢዜአ)፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና  44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ የምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ሰጠ።

በመርሃ ግብሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ፣የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። 

ስብሰባው"ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አፍሪካዊ ማስተማር፤ የማይበገሩ የትምህርት ስርዓቶች በመገንባት በአፍሪካ ሁሉን አቀፍ፣የሕይወት ዘመን ጥራትና አግባብነት ያለው የትምህርት ተደራሽነትን ማስፋት“ በሚል መሪ ሃሳብ መካሄዱ ይታወሳል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ በዚሁ ጊዜ ፤37ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እና  44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚ የምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በከፍተኛ ቅንጅት በስኬት መጠናቀቁን  አስታውሰዋል ።

በሕብረቱ  ስብሰባ ከ8 ሺህ በላይ እንግዶች ተሳትፈው  በሰላም ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም የብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች፣የጸጥታ አካላት ፣የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ስብሰባው በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች ለማስከበር የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም