የአፍሪካ አገራት ለቅድመ አደጋ መከላከል ስራ የተለየ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል -  የአፍሪካ ሕብረት 

65

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ አገራት የቅድመ አደጋ መከላከል ላይ አበክረው በመስራት በአደጋ የሚመጣ ጉዳትን መቀነስ እንደሚኖርባቸው የአፍሪካ ሕብረት አሳሰበ።

አገራቱ ለአደጋ መከላከልና ምላሽ የሚመድቡትን የገንዘብ መጠን ማሳደግ እንደሚኖርባቸውም አመልክቷል።

14ኛው የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ተቋም ስምምነት (ARC Treaty) ፈራሚ አገራት የሚኒስትሮች ስብሰባ ዛሬ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄዷል።

በስብስባው ላይ የተቋሙ አባል አገራት አመራሮችና ባለሙያዎች፣የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍል አመራሮች፣የአፍሪካ አገራት የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሮች፣የልማት አጋሮችና የዘርፉ ተዋንያን ተካፍለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍል የዘላቂ ከባቢ አየር ዳይሬክተር ሀርሰን ንያምቤ ሀርሰን አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለተለያዩ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተጋለጠች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ሕብረቱ የሚደርሱ አደጋዎችን ቀድሞ መከላከልና የድህረ አደጋ ምላሽ አቅምን ማጎልበት ላይ ከአባል አገራት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ የቅድመ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በመገንባት አገራት ከማዕከሉ በሚያገኙት የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ድህረ አደጋ ምላሽን መሰረት ያደረገ የመከላከል ስራ ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የአፍሪካ አገራት ለቅድመ አደጋ መከላከል ስራ የተለየ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብለዋል።

በተለይም አገራት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት በመዘርጋት የአደጋ ስጋት አስተዳደር አቅማቸውን ማጎልበት እንደሚኖርባቸው ነው ያሳሰቡት።


 

የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ዳይሬክተር ጀነራል ኢብራሂማ ቼክ ዲዮንግ ተቋሙ የአፍሪካ ሕብረት ካስቀመጣቸው ስትራቴጂዎችና ግቦች ጋር የተጣጣመ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የሚመጡ አደጋዎችና የበሽታዎች ክስተትን አስቀድሞ የመከላከልና የዝግጁነት አቅም ማጎልበት ላይ በዋናነት እየሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የአፍሪካ አገራት ለአደጋ ስጋት አስተዳደር የሚመድቡትን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በተጨማሪም አገራቱ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ዙሪያ ያላቸውን ተሞክሮ መለዋወጥና በትብብር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ አገራት የተቋሙ አባል አገር በመሆንና የማቋቋሚያ ስምምነት በመፈረምና በማጽደቅ ተሳትፏቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የሶማሊያ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር ካዳር ሼክ መሐመድ ሶማሊያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ አደጋዎችን አስቀድሞ በመከላከልና የአደጋ ስጋትን መቀነስ ላይ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።


 

የዛምቢያ የቀድሞ የግብርናና የእንስሳት ሀብት ምክትል ሚኒስትር ቻንስ ካባጌ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች መደገፍና ምርታማነታቸውን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በዛምቢያ የሚገኙ አርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል። 

የልማት አጋሮች ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና እና የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

14ኛው የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ተቋም ስምምነት (ARC Treaty) ፈራሚ አገራት ስብስባ በባለሙያዎች ደረጃ ትናንትና ዛሬ ከቀትር በፊት ሲካሄድ ቆይቷል። 

በስብሰባው ሌሴቶ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ቢሮ ሊቀ መንበርነትን ከሶማሊያ የተረከበች ሲሆን ሊቀ መንበርነቷ ለአንድ ዓመት ይቆያል።

የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ እ.አ.አ በ2012 የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ 39 አባል አገራት አሉት።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም