በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የንጹህ ውሃ  አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ  የባለድርሻ አካላት ድጋፍ  እንዲጠናከር ተጠየቀ

101

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 15 / 2016(ኢዜአ)፡-  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለህብረተሰቡ  ለማዳረስ በሚደረግ ጥረት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጠል ተጠየቀ፡፡

በክልሉ ኡንዱሉ ወረዳ በ56 ሚሊዮን ብር የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የክልሉ ውሃ እና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መሃመድ ሃምደኒል እንዳሉት፤  በክልሉ የህብረተሰብ ዋነኛ የልማት ጥያቄ ከሆኑት አንዱ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በተለይም ቆላማ በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች የመጠጥ ውሃን ለማዳረስ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡

ሆኖም  ንጹህ የመጠጥ ውሃን የማዳረስ ስራ በአቅም ውስንነት ምክንያት ሰፊ ርብርብ እንሚጠይቅ ገልጸው፤  በዚህ ረገድ የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ለበቁት የውሃ ተቋማት ድጋፍ ላደረገው ፋሮ ፋውንዴሽን ለተባለው ድርጅት  ምስጋና ያቀረቡት አቶ መሃመድ ፤  የአካባቢው ህብረተሰብ የውሃ ተቋማቱን በመንከባከብ ረጅም አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡


 

በኢትዮጵያ የፋሮ ፋውንዴሽን ተወካይ ዶክተር ኤርሚያስ ሃብቴ ድርጅቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሁለተኛ ደረጃ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በሆሞሻ ወረዳ  በመክፈት የድርሻውን አስተዋጽኦ እያረከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማትን በማስፋፋት እና ግብርናውን የሚደግፉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


 

በድርጅቱ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በጋሻው ተሾመ በበኩላቸው ዛሬ የተመረቁት የመጠጥ ውሃ ተቋማት በክልሉ አሶሳ ዞን ኡንዱሉ ወረዳ ከ15 ሺህ 500 በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላላ ግምታቸው 56 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡


 

የንጹህ መጠጥ ውሃ  ተጠቃሚ ከሆኑት የወረዳው ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ጊሴማ የሱፍ  በሰጡት አስተያየት የመጠጥ ውሃ ተቋሙ መገንባት ውሃ ፍለጋ የሚባክነውን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ ለሌላ ስራ ለማዋል እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም