በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ልማት አቅምን አሟጦ በመጠቀም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው

62

ዲላ ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ልማት ዘርፍ ያለውን አቅም አሟጦ ለመጠቀም በተከናወኑ ሥራዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይለማርያም ተስፋዬ የክልሉን የግብርና ልማት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት በክልሉ በዓመት ሦስት ጊዜ የማምረት አቅም እንዳለ ታይቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

በመስኖ ልማት ከዕቅድ በላይ 129 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ  የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ዋጋ የማረጋጋት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በበልግ እርሻ ከ797 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት መታቀዱንና እስካሁንም ከ669 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በልማቱ አርሶ አደሩን በነቂስ እንዲሳተፍ መደረጉን ገልጸው፣ የታቀደውን ለማሳካት ቀሪ መሬቶችን በዘር ለመሸፈን እና የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሌማት ትሩፋት መርሀግብር በሀገር ደረጃ በክልሉ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ በላቀ ትጋት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለእዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በክልል ደረጃ 1ሺህ 738 የወተት፣ የዶሮ፣ የንብ እና የአሳ መንደሮች መመስረታቸውን አቶ ሃይለማርያም ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ74 ሺህ በላይ የዳልጋ ከብቶችን በተሻሻሉ ዝርያዎች የማዳቀልና ከ382 ሺህ ቶን በላይ የወተት ምርት መገኘቱን ጠቁመው፣ ይህም ካለፉት ዓመታት አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

እንደ ሃላፊው ገለጻ በክልሉ በተያዘው ዓመት በተፋሰስ ልማት ከ153 ሺህ 300 ሄክታር በላይ መሬት በዘመቻ ለምቷል።

በተለይ ተራራማ አካባቢዎችን ወደምርት ለማስገባት በተከናወኑ ሥራዎች ከ10 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር በላይ የጤረጴዛ እርከን መሰራቱን ነው ያስረዱት።

በቀጣይ በተፋሰስ ልማት የታቀፉ ተራራማ አካባቢዎች ላይ ወጣቶችን አደራጅቶ ወደሥራ በማስገባት  ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ሃይለማርያም አስረድተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም