ውድድሩ የስታርት አፖች የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሃሳብ ጥቅም ላይ እንዲውል  ያስችላል-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

50

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ ከስታርት አፕ ኢትዮጵያ አውደ ርዕይ  ጎን ለጎን  የሚከናወነው ውድድር የስታርት አፖች የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሃሳብ ጥቅም ላይ እንዲውል ያስችላል ሲል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ የኢትዮጵያ "ስታርት አፕ" አውደ ርዕይ በሳይንስ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት መደረጉ ይታወቃል።

ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎን የስታርት አፖች የፈጠራ ሃሳብ ውድድር እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስታርት አፖች ድጋፍ ኃላፊና የውድድሩ ዳኛ አቶ ታደሰ አንበሴ እንደገለጹት የስታርት አፖች የፈጠራ ሃሳብ ውድድር የአውደ ርዕዩ አካል ሲሆን 90 ተወዳዳሪዎች ቀርበውበታል።

ከእነዚህ ውስጥ የተሻለ ሃሳብ ያላቸው 20 ስታርት አፖች ለውድድር ተለይተው ለመጀመሪያ ዙር የመወዳደሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

በቀጣይም ምርጥ አስሮችን በመለየት የፈጠራ ሃሳባቸው ስራ ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ሽልማትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

የውድድሩ ልየታ በቀጣይ የሚከናወን ሲሆን ፍጻሜው በአውደ ርዕዩ ማጠናቀቂያ እለት እንደሚደረግም አክለዋል።

ውድድሩ የስታርት አፖች የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሃሳብ ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ባሻገር ለተሻለ ስራ እንዲነሳሱ የሚረዳቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዘርፉ መስራት ከሚፈልጉ ባለሃብቶችና ስታርት አፖች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል።

ለውድድር የቀረቡት ሃሳቦች ቴክኖሎጂያዊ አሰራሮችን እውን የሚያደርጉና የማህበረሰቡን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያቃልሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የውድድሩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት መንግስት ለስታርት አፕ የሰጠው ትኩረት የፈጠራ ስራዎችን ወደ ተግባር ለማስገባት እድል የሚፈጥር ነው።

በተጨማሪም አውደ ርዕዩ በዘርፉ የተከናወኑ ስራዎችን ለማስተዋወቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያግዝም አንስተዋል።

ውድድሩ የፈጠራ ሃሳባቸውን ይበልጥ በማዳበር ችግር ፈቺና ዘመናዊ የአኗኗር ስልት እውን እንዲሆን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

በተለይም ያላቸውን አቅም በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለመፍጠርም ውድድሩ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አንስተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም