በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደልማት ገብተዋል

60

አርባ ምንጭ ፤ሚያዚያ 15/2016 (ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት ጥያቄ ያቀረቡ 124 ባለሀብቶች መሬትና ፈቃድ ወስደው ወደልማት መግባታቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

ቢሮው የበጀት ዓመቱን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ አካሂዷል። 

የቢሮ ሃላፊው ዶክተር ኦንጋዬ ኦዳ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ናቸው። 

ባለሃብቶቹ ከተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ኘሮጀክቶች መካከል ግብርና፣ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፍ ይገኙበታል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥት መሰረተ ልማት የተሟላለት ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማቅረብ ለባለሀብቶቹ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቁመዋል።

ኢንቨስትመንቶቹ ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ዶክተር ኦንጋዬ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደልማት በገቡና በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ከ30ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠራቸውንም አስታውቀዋል።

በክልሉ ሰፊ  የእርሻ መሬት፣ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት፣ ተስማሚ የአየር ጸባይ እንዲሁም  መሠረተ ልማት መኖር ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ እየጨመረ መምጣት አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ባለሀብቶች ወደ ክልሉ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ራሳቸውንም ክልሉንም ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል።

 


የወላይታ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ መሪሁን መና ኢንቨስትመንት ለውጪ ምንዛሬ ግኝት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

አቶ መሪሁን እንዳሉት፣ ዘርፉ ለማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በክልሉ ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዚህ ረገድ በዞኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ሥራዎች 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ ከ20 በላይ ፕሮጀክቶች ፍቃድ ወስደው ወደ ተግባር መግባታቸውንም ጠቅሰዋል። 

ባለሀብቶቹ በገቡት ውል መሠረት እንዲያለሙ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። 


 

የደቡብ ኦሞ ዞን ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ሎቱሩሲ ካረ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ በዘመናዊ ግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ለአካባቢው ልማት መጠናከር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው።

ከእዚህ በተጨማሪ ለአርሶና አርብቶ አደሮች የቴክኖሎጂ ሽግግር እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይ ከ300 በላይ አርብቶ አደሮች በዚህ ዓመት ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ በማድረግ ወደ ግብርና ልማት እንዲገቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነው ያስታወቁት።

በዞኑ የኦሞ፣ የወይጦና ናማኪ ወንዞች ለግብርና ኢንቨስትመንት ልማት አመቺ መሆናቸውን ለአብነት የጠቀሱት መምሪያ ሃላፊው፣ በተለይ ኦሞ ወንዝ በክረምት የሚያስክተለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ወንዙን ለኢንቨስትመንት፣ ለመካከለኛና መለስተኛ መስኖ ልማት ለማዋል እየተሠራ መሆኑን አስታውሰዋል።


 

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የግምገማ መድረክ ላይ ከ12 ዞኖች የተውጣጡ የኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም