የምግብ ዋስትናና የአየር ንብረት ለውጥን የተመለከተ አህጉራዊ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

165

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2016(ኢዜአ)፦  የምግብ ዋስትናና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልን የተመለከተ አህጉራዊ  የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

መድረኩ“ለአየር ንብረት ለውጥ ቴክኖሎጂ  ተኮር መፍትሔዎች  እና በአፍሪካ ለምግብ ዋስትና የማይበገር አቅም መገንባት፤ እድሎችና ፈተናዎች” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

14ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (UNFCCC) የአፍሪካ ፈራሚ አገራት ስብስባ (COP 14) በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ከስብስባው ጎን ለጎን የአፍሪካ የምግብ ስርዓቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን የተመለከተ የምክክር መድረክ  ነው።

በመድረኩ ላይ የአፍሪካ ሪስክ ካፓሲቲ ዳይሬክተር ጀነራል ኢብራሂማ ቼክ ዲዮንግ፣ የአፍሪካ ሕብረት የግብርና፣ የገጠር ልማት፣ “ብሉ ኢኮኖሚ” እና ዘላቂ ከባቢ አየር የስራ ክፍል አመራሮች፣ የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ለማና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የሌሎች የአፍሪካ አገራት የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮችና የዘርፉ ተዋንያን ተገኝተዋል።

የምክክር መድረኩን ያዘጋጁት የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተቋም የሆነው የአፍሪካ ሪስክ ካፒሲቲ(ARC)፣ከግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስቲትዩትና የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ነው።

በውይይቱ የአፍሪካ አገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በመገንባት፣ የግብርና የገበያ ትስስርን ማጠናከር፣ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍና ዓለም ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አኳያ የግብርና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎችን እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራትና በገጠሟቸው ፈተናዎች ላይ ምክክር እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

ስብስባው ትናንት በባለሙያዎች ደረጃ መካሄዱ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም