በመደመር ትውልድ መጽሐፍት ሽያጭ የተገነቡ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳዎች ተተኪዎችን ለማፍራት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው

244

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 13/2016(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ በመደመር ትውልድ መጽሐፍት ሽያጭ የተገነቡ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳዎች ለታዳጊዎች የኳስ ብቃትና ክህሎት ጥሩ መሰረት እየጣሉና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትም አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አሰልጣኞች ገለጹ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተፃፈው የመደመር ትውልድ መጽሐፍ ተሽጦ ገቢው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለልማት ሥራ እንዲውል ተደርጓል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በመዲናዋ የእግር ኳስ፣ የፉት ሳል፣ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ፣ የሜዳ ቴኒስና ሌሎች የመጫወቻ ስፍራዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው።

በመደመር ትውልድ መጽሐፍት ሽያጭ ተገንብተው ወጣቶችና ታዳጊዎች እየተጫወቱባቸው ከሚገኙ የእግር ኳስ ሜዳዎች መካከል የኢዜአ ሪፖርተር በመዘዋወር አሰልጣኞችና ሰልጣኞችን አነጋግሯል።


 

በፈረንሳይ 41 ማዞሪያ ራስ ካሣ ሜዳ እና በልደታ ክፍለ ከተማ ቢሊሞ ሜዳ ልምምድ ሲያሰሩ ያገኘናቸው አሰልጣኝ ሰላምሰው ምዳ፤ መደመር በስፖርቱ ዘመን ተሻጋሪ አሻራ እያሳረፈ መሆኑን ገልጸዋል።

በመደመር ትውልድ መጽሐፍት ሽያጭ የተገነቡ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳዎች ለታዳጊዎች የኳስ ብቃትና ክህሎት ጥሩ መሰረት እየጣሉና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራትም አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለዋል።


 

በራስ ካሣ ሜዳ በስልጠና ላይ ያገኘናቸው ይስሐቅ ኃይለማርያም እና አቤሜሌክ ኤርሚያስ፤ ከመገንባቱ በፊት ሜዳው ለጨዋታ አስቸጋሪና ለጉዳት የሚዳርግ እንደነበር አስታውሰው ከተገነባ በኋላ በብዙ መልኩ ደረጃውን የጠበቀና ለስልጠና ምቹ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በቢሊሞ ሜዳ ሲያሰለጥኑ ያገኘናቸው አሰልጣኝ መንግሥቱ አረጋ፤ የሜዳው በዘመናዊ መልኩ መሰራት የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚቀይሩ ልጆች ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።

በሜዳው ሲሰለጥኑ ያገኘናቸው ታዳጊ ልዑል ዮናስ እና ሰላዲን ሀሰን በዘመናዊ መልኩ አዲስ የተሰራው ሜዳ እኛን ጨምሮ ለበርካታ ልጆች ጥሩ የኳስ መሰረት እያስያዘ ነው ብለዋል።

በመዲናዋ ከሚገኙ 24 የስፖርት ማዘውተሪያዎች መካከል ሰባቱ ከመደመር ትውልድ መጽሐፍት ሽያጭ በተገኘ ገቢ የተገነቡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በመንግሥት በጀት የተሰሩ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም