ብሄራዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርአት ወጥ የሆነ ቀልጣፋና የተቀናጀ  አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው

195

አዲስ አበባ  ፤ ሚያዚያ 13 /2016(ኢዜአ) ፡ ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ወጥ የሆነ ሀገራዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በመዘርጋት የተቀናጀ፣ ቀልጣፋና የተረጋገጠ  አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት ማለት መሠረታዊ የሆኑ የግል ዲሞግራፊክ እና ተፈጥሯዊ የሆነውን የዓይን፣ የጣትና የፊት የባዮሜትሪክ መረጃዎችን መዝግቦ በመያዝ በማዕከላዊ ቋት የሚያስቀምጥ አሠራር ነው።

የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከተከናወነ በኋላ ልዩ ቁጥር በመስጠት ተመዝጋቢው የተደራጀና አስተማማኝ የዲጂታል መታወቂያ እንዲኖረውም ያደርጋል።

የዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ለሰላምና ደኅንነት፣ ለተፋጠነ ልማት፣ የምጣኔ ኃብት ሽግግርና መልካም አስተዳደር የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ይታወቃል።

የፖሊሲ ቀረፃን፣ የምጣኔ ኃብትና ማኅበራዊ ልማት ክንውንን አካታች ለማድረግም እንዲሁ።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሐሚድ ኪኒሶ፤ የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ወቅቱን የዋጀ ለሀገርና ሕዝብ የሚጠቅም ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት መሆኑን ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ አንድ ወጥ የሆነ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በመዘርጋት የተቀናጀ፣ ቀልጣፋና የተረጋገጠ   አገልግሎት ለመስጠት የላቀ ጠቀሜታ የሚኖረው መሆኑን ተናግረዋል።

የውል ስምምነቶችና ሌሎችንም ሰነዶች በማጣራት በቴክኖሎጂ የታገዘ ምዝገባና ማረጋገጫ የሚደረግበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በ15 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በየቀኑ በአማካይ ለ6 ሺህ 500 ሰዎች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከመታወቂያ ጋር በተያያዘ ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰው፤ የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ግን ጥራት ያለው ቀልጣፋና የተቀናጀ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

የዲጂታል መታወቂያ ለተቋሙ አገልግሎት መሳለጥ ወሳኝ በመሆኑ ተቋማቸው ከብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) ጽህፈት ቤት ጋር በመቀናጀት እየመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም እስካሁን ከ70 ሺህ 300 በላይ ተገልጋዮችን ለብሄራዊ መታወቂያ መመዝገብ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም