የኢትዮ-ኤርትራ የእርቀ ሰላም ጅምር የሚበረታታ ነው - አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት

78
አዲስ አበባ ሰኔ 15/2010 ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ ሠላም ለማምጣት ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑን የአሜሪካ መንግሥት ገለጸ። የአውሮፓ ኅብረትም አገራቱ ሰላም ለማምጣት የወሰኑት ውሳኔ ከሁለቱ ሕዝቦች አልፎ ለአፍሪካ ቀንድ ጠቃሜታው የጎላ መሆኑን አስታውቋል። የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ፤ በአገራቱ መካከል ባለፉት 20 ዓመታት የነበረው ግጭት በቀይ ባህር አካባቢ መረጋጋት እንዳይኖር አድርጓል። በተጨማሪም በአካባቢው ምጣኔ ኃብታዊ እድገት እንዳይመዘገብ ማገዱንም ነው መግለጫው የጠቆመው። ይሁንና በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ያለውን የቆየ አለመግባባት ለመፍታትና ግንኙነታቸውን መደበኛ ለማድረግ ያሳዩት ቁርጠኝነት ይበረታታል ብሏል የአሜሪካ መግለጫ። ዘላቂ ሰላም ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራት፣ ለአሜሪካ እንዲሁም ለዓለም ጭምር ደህንነትና ዕድገት መሆኑን በመጠቆም። የኢትዮጵያ መንግሥት በአዎንታዊ የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ማሻሻያ አውድ በመቃኘት የአልጀርሱን ሥምምነት ተቀብሎ መወሰኑን አሜሪካ አወድሳለች። ይህን ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የሠላም ሂደቱን ከግብ ለማድረስ ወደ ኢትዮጵያ ልዑክ እልካለው ማለታቸውንም መግለጫው በአዎንታ ተመልክቶታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ኢሳይያስ አፈወርቂ ሰላም ለማምጣት ለወሰዱት አበረታች የመሪነት ሚና አሜሪካ አድናቆቷን ቸራቸዋለች። ኢትዮጵያና ኤርትራ በአቀፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት ለማምጣት ትልቅ ሚና እንዳላቸው የገለጸው መግለጫው አሜሪካ ከአገራቱ ጎን እንደምትቆም አረጋግጧል። ይህም ደግሞ አገራቱ ግንኙነታቸውን ወደ መደበኛው በመቀየር የጋራ የሚሉት ሰላምና ልማት እስኪሰፍን ድረስ አሜሪካ አብራቸው እንደምትሆን ነው መግለጫው የጠቆመው። የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ፍሬድሪካ ሞግሄሪኒም በቅርቡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥት የተወሰደው የሰላም እርምጃ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል። እርቀ ሰላም መውረዱ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው መረጋጋት ጭምር ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው ኅብረቱ ከጎናቸው እንደሚቆም አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ አገራቱ ሰላም ለማውረድ ያደረጉት እንቅስቃሴ በመካከላቸው ሰላም በማስፈን ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካም ጠቃሚ መሆኑን የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሪክሰን ሶሬይድ ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም