ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 1 ሺህ 835 አቤቱታዎች ላይ  የውሳኔ ሀሳብና ውሳኔ  ተሰጥቷል- የህገ መንግስት  ጉዳዮች  አጣሪ  ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፦  በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ከ1ሺህ 835  በላይ  አቤቱታዎች ላይ የውሳኔ ሀሳብና ውሳኔ  መስጠቱን የህገ መንግስት  ጉዳዮች  አጣሪ  ጉባኤ  አስታወቋል።

የጉባኤው  የቦርድ ሰብሳቢ  እና  የፌዴራል  ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት  ቴዎድሮስ ምህረት የጉባኤውን  የ2016  በጀት ዓመት አፈፃፀም አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ከተለያዩ  ተቋማት፣ ከቡድኖችና ግለሰቦች  923 አቤቱታዎችን መቀበሉን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ተራቸውን  ሲጠብቁ የነበሩ አቤቱታዎችን ጨምሮ  1 ሺህ 835 አቤቱታዎች  ላይ ተወያይቶ   የውሳኔ  ሀሳብና ውሳኔ  መስጠቱን ተናግረዋል።

ከዚሁ ውስጥ  1 ሺህ 686 አቤቱታዎች  የህገ- መንግሥት  ትርጉም አያስፈልጋቸውም በማለት  ውሳኔ  የተሰጠባቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

24  አቤቱታዎች  ደግሞ የህገ- መንግሥት  ትርጉም ያስፈልጋቸዋል  በሚል  ውሳኔ እንደተሰጠባቸው  ገልጸው፥ 125ቱ ደግሞ ተጨማሪ መረጃ እንዲሰበሰብባቸውና እንዲጠኑ መወሰኑን አብራርተዋል።

ለአጣሪ ጉባኤው  የሚቀርቡ  አቤቱታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ  እየጨመሩ  መምጣታቸውን  ጠቁመው ጉባኤው  በሰው ሃይልና በአደረጃጀት ራሱን በማጠናከር ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። 

በቀጣይም  አቤቱታ  አቅራቢዎች  በቴክኖሎጂ ታግዘው ካሉበት  ቦታ  አቤቱታ  የሚያቀርቡበትን አሰራር ለመዘርጋት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም