የኢፌዴሪ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያስችለው የአሰራር ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ ደንብ አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢፌዴሪ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሥራውን ለማቀላጠፍ የሚያስችለው የአሰራር ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ ደንብ አዘጋጀ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2016 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችና አቤቱታዎች የማጣራት ሥራን በፍጥነትና በግልፅነት ለመተግበር የሚያስችለውን የአሰራር ሥነ-ሥርዓት ረቂቅ ደንብ አዘጋጀ።
የኢፌዴሪ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባዘጋጀው የአሰራር ሥነ-ሥርዓት ደንብ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እያካሄደ ነው።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንትና የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ምክትል ሰብሳቢ አበባ እምቢአለ ደንቡ የሕገ-መንግሥት የበላይነትን ለማስከበር ይጠቅማል ብለዋል።
የሕገ-መንግሥት ትርጉም ጥያቄዎችና አቤቱታዎች የማጣራት ሥራን በፍጥነት፣ በግልፅነትና ለተገልጋይ ቀላል በሆነ መልኩ ለመተግበር ደንቡ እንደሚያግዝም ነው ያብራሩት።
ጎን ለጎንም ደንቡ የጉባዔውን አሠራር ወጥ ለማድረግ እንዲሁም አጠቃላይ የሕገ-መንግሥት አተረጓጎም ሥርዓቱን የተሻለ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ጉባኤው ሥራውን ከጀመረበት ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ ከተለያዩ ተቋማት፣ ቡድኖች፣ ግለሰቦችና ፖለቲካ ፓርቲዎች ከ8 ሺ በላይ አቤቱታዎችን ተቀብሏል ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ በ4 ሺህ 340 መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠቱንና የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡን ጠቅሰዋል።
የኢፌዴሪ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 84 መሰረት ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን የተሰጠው መሆኑ ይታወቃል።