በኦሮሚያ ክልል አገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎችን ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል አገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎችን ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ሰኔ 2/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል አገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎችን ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቢሮው ኃላፊ ቶላ በሪሶ (ዶ/ር) በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ ስራዎችን እንዲሁም አገር አቀፍና ክልል አቀፍ ፈተናዎችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫውም ተማሪዎች የተሳካ የፈተና ጊዜ እንዲኖራቸው ዘርፈ-ብዙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።
ኃላፊው እንዳሉት፥ በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ በኦሮሚያ ክልል ከ202 ሺህ በላይ ተማሪዎች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን ከ547 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሚወስዱ ሲሆን በ8ኛ ክፍል ፈተና ላይ ደግሞ ከ430 ሺህ በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ አክለው ገልጸዋል።
የፈተናዎችን የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተም የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና ከሰኔ 8 እስከ 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የ8ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ ሰኔ 11 እና 12 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
ተማሪዎች መፈተን የሚችሉባቸውን ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተማሪዎች መማር ያለባቸውን የትምህርት ይዘቶች ሙሉ በሙሉ እንዲሸፍኑ ማድረግና ለተማሪዎቹ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት ዋነኞቹ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና የበይነ-መረብ (Online) ተፈታኞች የኮምፒውተር ልምምድ እንዲያደርጉ መደረጉ ከተሰሩ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።
የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና በአብዛኛው በበይነ-መረብ የሚሰጥ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ ለዚህም ስኬታማነት አስፈላጊው የግብዓት እና የመሠረተ-ልማት አቅርቦት የተሳለጠ እንዲሆን የተለያዩ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስገንዝበዋል።
ልዩ ድጋፍ ለሚሹ ተፈታኝ ተማሪዎችም ምቹ የመፈተኛ አካባቢን ለመፍጠር ቢሮው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።