ቀጥታ፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጥራትን  ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ ትውልድ የማፍራት ስራ እየተከናወነ ነው

ድሬደዋ/ሐረር፣ ሰኔ 2/2018(ኢዜአ) ፡- በሐረሪ ክልል እና ድሬደዋ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጥራትን  ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ ትውልድ የማፍራት ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ።

በሐረሪ ክልል እና ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍና አስተዳደር አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀመረ።

በሐረሪ ክልል የተጀመረውን የ6ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተመልክተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ነገዎ በወቅቱ  እንዳሉት፤ የትምህርት ጥራትን ወደ ተሻለ ደረጃ በማሳደግ እና ተማሪዎችን በማብቃት ኩረጃን የሚፀየፍ ትውልድ ለማፍራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በክልሉ 6ሺህ 418 ተማሪዎች ለፈተናው መቀመጣቸውን ገልጸው፤ ተማሪዎቹን ለፈተናው ብቁ ለማድረግ የማጠናከሪያ ትምህርት ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ሞዴል ፈተናዎችን በመስራት እንዲለማመዱ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱም አመልክተዋል።

በክልሉ ፈተናው በ19 የገጠር እና 13 የከተማ፤ በድምሩ በ32 የፈተና ጣቢያዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ  ተናግረው፤ ዛሬ ለፈተና የተቀመጡት 2ሺህ 684 ወንዶች እና 3ሺህ 734 ሴቶች በድምሩ 6ሺህ 418 ተማሪዎች መሆናቸው አክለዋል።


 

በተመሳሳይ በዴሬደዋ አስተዳደርም የ6ኛ ክፍል አስተዳደር አቀፍ ፈተና መሰጠት ተጀምሯል።

ፈተናውን በመፈተኛ ጣቢያዎች ተገኝተው ያስጀመሩት የድሬደዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሱልጣን አልዪ እና የቢሮው የስራ ሃላፊዎች ናቸው።

አቶ ሱልጣን በወቅቱ እንደገለፁት፤ በመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት እርከን የትምህርት ተደራሽነትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ተግባራት አበረታች ናቸው።

በትምህርት ለትውልድ  ንቅናቄ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት እና በማስፋፋት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ እንዳይለዩ መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።


 

በተለይም በገጠርና በከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ መርሃግብርን ከአጋር አካላት ጋር በስፋት ማካሄዱ ተማሪዎች ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ እና ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ዛሬ በተጀመረው አስተዳደር አቀፍ የ6ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተገኙ 8ሺህ 100  ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡም ያላቸውን እምነት  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም