ቀጥታ፡

በአርባ ምንጭ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከጎበኙ ቱሪስቶች ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኘ

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 2/2018 (ኢዜአ)፡-በአርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን ከጎበኙ የሀገር ወስጥና የውጭ ቱሪስቶች ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የከተማው ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

ከተማዋን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራትም ውጤት መመዝገቡ ተመላክቷል። 

የአርባ ምንጭ ከተማ ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ደምበላ ለኢዜአ እንደተናገሩት በከተማው አርባ ምንጮች፣ ዓባያና ጫሞ ሐቆችን፣ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ፣ አዞ ራንችና ሌሎች መዳረሻዎች በስፋት ይገኛሉ።


 

ቱሪስቶች የሚያርፉባቸው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶች፣ ሎጆችና ሆቴሎች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ ደስታ በበጀት ዓመቱ ብቻ አራት ዓለም አቀፍ ሆቴሎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በበጀት ዓመቱ እስካሁን ድረስ ከ320 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ከተማዋን እንደጎበኙና ከዚህም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻዎች እየለሙ መሆናቸው ገልጸው፣ በዚህም ከጋሞ ልማት ማህበር ጋር  በመቀናጀት የተከናወኑ ተግባራት ከተማዋን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል እያደረጋት ይገኛል ብለዋል።


 

የጋሞ ልማት ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ማንደፍሮት ዱባለ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት ልማት ማህበሩ በበጀት ዓመቱ በዓባያ ሐይቅ ላይ የሚገኙ 11 ደሴቶችን የሚያስተሳስር የጀልባ ትራንስፖርት አገልግሎት ጀምሯል።

በከተማው ግርጌ በአንድ ስፍራ የሚገኙ 40ዎቹ ምንጮችን ለመመልከት ለሚመጡ ቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም "አርባ ፤ አርባ ሁለት" የተሰኘ 1ሺህ 680 ደረጃ ያለው መንገድ መገንባቱን ገልጸዋል።

ለጉብኝት ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ከመጡ ቱሪስቶች መካከል ከአዲስ አበባ እንደመጣ የተናገረው ወጣት ታደለ ግዛት በከተማዋ የተለያዩ መዳረሻዎችን መጎብኘቱን ተናግሯል።


 

አርባ ምንጭን ጨምሮ በሀገራችን ሊጎበኙ የሚገባቸው ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች እንዳሉ ገልጾ፣ ኢትዮጵያውያን እነዚህን የቱሪዝም ሀብቶች የመጎብኘትና የማወቅ ባህል ልናዳብር ይገባል ብሏል።

አርባ ምንጭና አካባቢዋ ልዩ የተፈጥሮ ሀብት የተቸረ በመሆኑ ቀልብን ይማርካል ያለው ደግሞ ከፖላንድ የመጣው ጎብኚ ሚስተር ባርተክ ሮማን ነው።

በአርባ ምንጭና አካባቢው የሚገኙ 40 ዎቹ ምንጮች፣ ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም ዓባያና ጫሞ ሐይቆችን በመመልከት መደሰቱን ገልጿል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም