ቀጥታ፡

ወልድያ የሰላም፣የመረጋጋትና የፈጣን ልማት ተምሳሌት ከተማ ሆናለች-አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ሰኔ 2/2018 (ኢዜአ)፦የወልድያ ከተማ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ ከተማዋ የሰላምና የኢኮኖሚ ልማት ተምሳሌት እንድትሆን ማስቻሉን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) ገለጹ።

በጦርነትና በተለያዩ የሰላም እጥረት ፈተናዎች የጉዳት ሰለባ ሆና የቆየችው ወልድያ ከተማ፣ በአሁኑ ወቅት እያስመዘገበችው ባለው ፈጣን የኮሪደር ልማትና ዘመናዊነት የክልሉ ከተሞች የብልጽግና ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷንም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በወልድያ ከተማ ሰፊ የኮሪደር ልማት ስራዎችን በምሽት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

ወልድያ ያስመዘገበችው ለውጥ ለሌሎች ከተሞች ድንቅ ተሞክሮ እንደሚሆን ተናግረዋል።

​የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን( ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በሰሜኑ ጦርነትና በፅንፈኛ ቡድኖች ግጭት ምክንያት ጎስቁላ የነበረችው ወልድያ፣ ዛሬ ላይ የዘመናዊ ከተሜነት መገለጫ ሆናለች።

በወልድያ ከተማ ስንንቀሳቀስ የኮሪደር ልማት ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር ስራዎች ጭምር መሰራታቸውን ተመልክተናል ብለዋል።


 

ከተማዋና ነዋሪዎቿ ፈተናዎችን በፅናት መሻገራቸውን ጠቅሰው፤ የኮሪደር ልማቱ ህጻናት ከወላጆቻቸው ጋር በምሽት ጭምር በፋውንቴኖች አካባቢ ሲጫወቱ፣ ነዋሪዎችም ፊታቸው ላይ ደስታ እየተነበበ ሲዝናኑ መመልከት ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም፣ ይህ ለውጥ የመጣው በብልፅግና መንግስት የመደመር እሳቤ ከተሞች ሳይፈርሱና ታሪካዊ ይዞታቸውን ሳይለቁ፣ ዘመናዊና ጽዱ እንዲሆኑ በተነደፈው መርሃ-ግብር መሆኑን ገልጸዋል።

ሀሳቡን በተግባር ለተረጎሙት የከተማዋ አመራሮች፣ ባለሀብቶች፣ ህብረተሰቡና አካባቢውን በፅናት ለጠበቁት የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የጸጥታ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ጠላቶች ስራ አጥነትንና የኢኮኖሚ ችግርን እንደ ማገዶ ለመጠቀም ቢሞክሩም፣ የክልሉ መንግስት በ2018 በጀት ዓመት ተግባራዊ ማድረግ የጀመረው የ25 ዓመት የአሻጋሪ እድገትና ዘላቂ ልማት እቅድ ውጤት እያመጣ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢኮኖሚ እድገት፣ የስራ እድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ልማት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው ብለዋል።


 

የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ በበኩላቸው፥ የከተማዋ አመራር በጦርነት የቆሰለችውን ከተማ ለመቀየር በትልቅ ቁጭት መነሳቱን ገልጸዋል።

በከተማዋ አጠቃላይ 6 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ የተከናወነ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ​የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ፓርኮችና የፓርኪንግ ቦታዎች፣ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ የሆኑ ዘመናዊ ሼዶች፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶችን ያካተተ ነው ብለዋል።

አሁን ከተማዋን ውብ፣ ጽዱና ለነዋሪዎቿ የተመቸች ብቻ ሳይሆን፣ ጎብኝዎች ውለው የሚያድሩባት የሰሜን ኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ በተሳካ ሁኔታ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም