ቀጥታ፡

ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የማሽላ ዝርያዎችን አርብቶ አደሮች እያለሙ ነው

ሮቤ፣ ሰኔ 2/2018 (ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን ሀረና ቡሉቅ ወረዳ በበልግ አዝመራ ድርቅን በመቋቋም የተሻለ ምርት የሚሰጡ የተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎችን እያለሙ መሆናቸውን አርብቶ አደሮች ገለጹ። 

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት በበኩሉ፤ የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከ125 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የቆላ ግብርና ኢኒሼቲቭ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

በሀረና ቡሉቅ ወረዳ የመልካ አርባ ቀበሌ ነዋሪ አርብቶ አደር ሐጅ አወል አብዲ እንዳሉት፤ በአካባቢያቸው የዝናብ እጥረት መኖሩን ተከትሎ የሚከሰተውን ድርቅ ተቋቁመው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የማሽላ ዝርያዎችን በማልማት የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እየተጉ ነው። 


 

በመንግስት የቀረበላቸውን የተሻሻሉ የማሽላ ዝርያዎች በመጠቀም በሄክታር በአማካይ እስከ 30 ኩንታል ምርት ማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል።

ሌላኛው አርብቶ አደር አሊ ሱልጣን አህመድ በበኩላቸው፤ የማሽላ ዝርያው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ የአየር ንብረት መዛባትን ለመቋቋም እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። 

ይህ የማሽላ ዝርያ ለምግብነት ከማገልገሉም ባሻገር፣ ተረፈ ምርቱ ለእንስሳት መኖ በመሆን ድርቅን ለመቋቋም ከፍተኛ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የሀረና ቡሉቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀሰን በበኩላቸው፤ በወረዳው ድርቅን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጡ የማሽላ ዝርያዎችን ለአርብቶ አደሩ በማቅረብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሰፊ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት በወረዳው በማሽላ ሰብል እየለማ ካለው መሬት ውስጥ 3 ሺህ 300 ሄክታሩ በተሻሻሉ ዝርያዎች እየለማ መሆኑን አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።


 

የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ እንደገለጹት፤ በዞኑ በቆላማ አካባቢዎች በበልግ የምርት ወቅት ከ125 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ ይገኛል። 

ከዚህ ውስጥ ማሽላ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ቦሎቄ፣ በቆሎና ሌሎች ገበያ ተኮር የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በልዩ ኢኒሼቲቭ እየለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከዚህ የቆላ ግብርና ልማትም ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

መንግስት የቆላ ግብርናን ለማስፋፋትና የምግብ ዋስትናን በራስ አቅም ለመሸፈን የጀመረው ስራ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኃላፊው አመልክተዋል።

በባሌ ዞን በአጠቃላይ በበልግ የምርት ወቅት ከተሸፈነው ከ277 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት፣ ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም