ቀጥታ፡

በክልሉ የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ነው

ነገሌ ቦረና፣ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ተጠቃሚነት  ለማረጋገጥ የተከናወኑ   ተግባራት   ውጤት እያስገኙ መሆናቸው  ተገለጸ።

በምስራቅ ቦረና ዞን  ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነቡ የፊና መስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል፡፡


 

ፕሮጀክቶቹን የመረቁት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ሳዳት ነሻህ ናቸው፡፡

የክልሉ መንግስት የአርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  የቆላማና ዝናብ አጠር አካባቢዎች ዘላቂ ልማት እቅድ በመንደፍ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቋቋም እየሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም  የአረንጓዴ አሻራ  መርሀ ግብርን የማጠናከር፣ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራና  የበጋ መስኖ ልማትን በመተግበር  የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰራቱን አንስተዋል።

በክልሉ  የቆላማ አከባቢዎች   የአርብቶ አደሩን የመስኖ ልማትን ለማጠናከርና የእንስሳት መጠጥ ወሀ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የፊና ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግም  ጥረት  መደረጉን  ገልጸዋል፡፡

በምስራቅ ቦረና ዞን ዛሬ ለምርቃት የበቁት ፕሮጀክቶችም  የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ለማሳካትና  ለእንስሳት  ውሀ አቅርቦት  ይውላሉ   ብለዋል፡፡ 

በቀጣይም የክልሉ መንግስት ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን ለውጤት በማብቃት   የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በዘላቂነት   ለማረጋገጥ የሚያደረገውን  ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ ኢንጅነር አለሙ ረጋሳ በምስራቅ ቦረና ዞን  የአርብቶ አደሩን የመሰረተ ልማት ተደራሽነት ለማረጋገጥ በግንባታ ላይ  ከነበሩ ሶስት  የፊና መስኖ ፕሮጀክቶች  መካከል ሁለቱ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቁመዋል።

በዞኑ ሊበንና ጎሮ ዶላ ወረዳ በግንባታ ላይ ከነበሩት ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው  ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹም  በቆላማና ዝናብ አጠር አከባቢዎች የሚታየውን የድርቅ ተጋላጭነት በዘላቂነት ለመቋቋም፣ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና ለእንስሳት መጠጥ ውሀ አቅርቦት እንዲሁም  ለመኖ ልማት እንደሚውሉ አመላክተዋል። 

የክልሉ መንግስት ግንባታቸው ለተጠናቀቁት  የፊና መስኖ ፕሮጀክቶች 518 ሚሊዮን ብር ወጭ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቶቹ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሜትር ኪውብ የዝናብ ውሀ የመያዝ አቅም ያላቸው እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን በበኩላቸው  ፕሮጀክቶቹ ከ465 ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት አቅም አላቸው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹ አርብቶ አደሩን  በመስኖ ልማት በመሰማራት ተጠቃሚ  ከማድረግ ባሻገር  ከቀየው ሳይርቅ ለእንስሳቱ የመጠጥ ውሀ እንዲያገኝ የሚያስችሉት መሆኑን አመልክተዋል።

በዞኑ የሊበን ወረዳ ነዋሪ አቶ ቃሲም ገመዳ በበኩላቸው  የፕሮጀክቶቹ መገንባት የህብረተሰቡን  ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ  ጥያቄዎች የመለሱ  መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአካባቢው የተሰሩት  የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች  ቀደም ሲል  ለእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሀ ፍለጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያደርጉትን  እንቅስቃሴ እንደሚያስቀሩላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም