በክልሉ በፍራፍሬና በቡና ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል − ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በፍራፍሬና በቡና ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል − ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ወላይታ ሶዶ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ) ፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በፍራፍሬ እና በቡና ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በክልሉ በፍራፍሬ፣ በቡናና ሥራስር ተክሎች ልማት ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ተገኝቶባቸዋል።
በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑና ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በበጋ መስኖና በመኸር እርሻ ከ107 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬና በአትክልት መሸፈኑን ተናግረዋል።
በዋናነትም ሙዝ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ እና የደጋ ፍራፍሬ እንዲሁም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች መልማታቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በክልሉ ከ60 ሺህ ሄክታር ያልበለጠ የሙዝ ማሳ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ጥላሁን፣ በአሁኑ ወቅት በአራት እጥፍ አድጎ ከ240 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ተናግረዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ለፍራፍሬ ልማት ሽፋን እያደገ መምጣት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ጥላሁን ገለጻ በተያዘው ዓመት በፍራፍሬ የሚለማውን መሬት ሽፋን ለማሳደግ በተያዘ ዕቅድ በተለያዩ አካባቢዎች የሚተከሉ ከ25 ሚሊዮን በላይ የአቮካዶ፣ ማንጎ እና አፕል ችግኞች ተዘጋጅተዋል።
በማህበር የተደራጁ ወጣቶችም በፍራፍሬ ልማት፣ በግብይትና ማቀነባበር የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የገለጹት።
የቡና ልማትን ከማስፋፋት አንጻር ለቡና ምቹ በሆኑ ሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ልማቱ እየተከናወነ መሆኑን ያመለከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በጌዴኦ ዞን ቡናን ስፔሻላይዝድ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የቡና ልማቱን በጥምር ግብርና በማከናወን የአርሶ አደሩን ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራትም ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።
በክልሉ የቡና ልማቱን ለማስፋት በተያዘው ዕቅድ መሰረት ዘንድሮ ከተዘጋጁ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው የቡና ችግኞች አብዛኞቹ ባለፈው ሚያዝያ ወር መተከላቸውን ገልጸው፣ ቀሪዎቹ በቀጣይ ሐምሌ ወር ይተከላሉ ብለዋል።