ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ ተግባራት ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው- ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

ጎንደር ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ ።

የጎንደር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ዛሬ ተካሂዷል ።

ርእሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያጠናክሩና የሚያሳልጡ ተግባራት ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው ።


 

በክልሉ ግንባታው የተጀመረው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው ፓርኩ በክልሉ ዋነኛ የኢኮኖሚ ማእከል እንደሚሆንም አመልክተዋል ።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው በሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር በማፋጠን ረገድ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወሳኝ የእድገት ምሰሶዎች ናቸው ብለዋል።

የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የግብርና ምርት እሴት ጨምሮ ለሀገርና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ምቹ የኢኮኖሚ መሠረት የሚጥሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

ዛሬ ግንባታው የተጀመረው አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የአካባቢውን የግብርና ምርት በስፋት በመጠቀም ለአካባቢው አምራች አርሶ አደሮች ሰፊ የገበያ እድል የሚፈጥር እንደሆነም አመልክተዋል።

ፓርኩን በሂደት ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በማሳደግ እንደ ሀገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ለማሳለጥ ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፓርኩ ለግብርና ምርቶች የገበያ እድል በማመቻቸት ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም ለከተሞች ገቢ ማደግና ለቴክኖሎጂ ሽግግር የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

የአማራ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ብርሀኑ ጣምያለው ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ256 ሄክታር መሬት ላይ ግንባታው እንደሚካሄድ ገልጸዋል።


 

የፓርኩ ግንባታ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ የኢንቨስትመንት ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቁመው ስራ ሲጀምር ለ55 ሺህ ወገኖች ቋሚ እንዲሁም ከ200ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ጊዚያዊ የስራ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ፓርኩ በአመት ከአንድ ሚሊዮን ቶን በላይ ምርት የማቀናበር አቅም ሲኖረው እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጪ ምንዛሪ የሚያስገኝ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ ዞኑ ለአግሮ ኢንዱስሪዎች ግብአት የሚውል ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ጥጥ የመሳሰሉ የግብርና ምርቶች በስፋት የሚመረቱበት እንደሆነ ተናግረዋል ።


 

ኢንዱስትሪ ፓርኩ ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት አስተዋፅኦው የላቀ መሆኑንም አመልክተዋል።

በኢንዱስትሪ ፓርኩ የግንባታ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የፌደራል፣ የክልል እንዲሁም የጎንደር ከተማና የማእከላዊ ጎንደር ዞን አመራሮችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም