ቀጥታ፡

በዲላ ከተማ የተዘጋጀው "ቡኖ - ማላ" ኤክስፖ ምርቶችንና የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማስተዋወቅ አስችሏል

ዲላ፤ ግንቦት 16/2018 (ኢዜአ)፡-ከ40 በላይ የንግድ ተቋማትና አጋር አካላት ተሳትፈውበት በዲላ ከተማ የተዘጋጀው "ቡኖ - ማላ" ኤክስፖ ምርቶችን እና የኢንቨስትመንት እድሎችን ጭምር ለማስተዋወቅ መልካም እድል መሆኑ ተገለጸ።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደውን "ቡኖ - ማላ" ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር) በይፋ ከፍተውታል።


 

በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክትም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቁም እንስሳት ሃብት የሚታወቀው የጌዴኦ ዞን ምርታማነቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በቡና እና ሌሎችም የልማት መስኮች የተሰማሩ ከ40 በላይ የንግድ ተቋማትና አጋር አካላት የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ መሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።

በመሆኑም ኤክስፖው ምርትና አገልግሎትን እንዲሁም የኢንቨስትመንት እድሎችን ጭምር ለማስተዋወቅ መልካም ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።


 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማኑኤል ብሩ፤ በክልሉ የይርጋጨፌ፣ የኮቾሬና አማሮን ጨምሮ ሌሎችም አካባቢዎች የባለ ልዩ ጣዕም ቡና የሚመረትባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።
 
ቡናን በጥሬ ከመላክ ባለፈ በልዩ ጣዕሞች አዘጋጅቶ እሴት ጨምሮ በመላክ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን አንስተው፣ ኤክስፖው ጥሩ ተሞክሮ ለመቀመርና ምርቶችን ለማስተዋወቅ የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።



 
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በዞኑ በግብርና ልማት በተለይም በቡና፣ እንሰትና የቁም እንስሳት ሃብት እምቅ አቅም መኖሩን አንስተው ኤክስፖው ይህንኑ ይበልጥ ለማስተዋወቅ መልካም ዕድል ነው ብለዋል።
 
የጌዴኦ ዞን የባህላዊ መልከዓ ምድር ማዕከል መሆኑን አንስተው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለሚሰማሩ አካላት አዋጭ የገበያ ዕድል እንዳለም ተናግረዋል።

በዞኑ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ የተለያየ ደረጃ ያላቸው የቡና ምርቶችንም ወደተለያዩ የወጭ ሀገራት እንደሚላኩ ተናግረዋል።
 
የይርጋጨፌ ቡና ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ተወካይ ቤተልሔም ዳንኤል፤ ዩኒየኑ ጥራቱን የጠበቀ ጥሬ ቡና ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ባለፈ የውጭ ገዥዎችን መሰረት ያደረገ እሴት የተጨመረበት ቡና ለገበያ እያቀረበ መሆኑ አንስተዋል።
 
በተለይ በቀን ከዘጠኝ ኩንታል በላይ በራሱ ልዩ ጣዕም ተቆልቶና ተፈጭቶ የተዘጋጀ ቡና ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን አንስተው፣ በኤክስፖውም ተጨማሪ የገበያ ትስስር እየፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።
 
በቡና ንግድ በእሴት ሰንሰለቱ ያሉ ተዋንያንን መቀነስ ለትርፋማነት መሰረት መሆኑን ያነሱት ደግሞ ወልትአብንዶ የቡና አቅራቢ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ሽታዬ ሃጥያ ናቸው።
 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም