በኦሮሚያ ክልል የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የአሰራር ማሻሻያና ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ የአሰራር ማሻሻያና ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል
አዳማ፤ግንቦት 16/2018(ኢዜአ)፦በክልሉ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ለአሰራር ማሻሻያና ለተቋማት ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ገለፁ።
በክልሉ ምስራቅ ሸዋ ዞን በቴክኖሎጂ የተደራጀ የአስተዳደር ህንፃ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በወቅቱ እንደገለፁት፥ የክልሉ መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ የአሰራር ማሻሻያና በተቋማት ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው።
የህዝቡን የልማት ጥያቄዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት ለመፍታት የቀበሌ አደረጃጀትን በቅርበት በመዘርጋት የአገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ላይ መሰራቱን አስታውሰዋል።
ይህም ህዝቡ አገልግሎቱን በቅርበት በማግኘት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቱን እንዲያፋጥን ከማስቻሉም በላይ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን መፍታት መቻሉን አመልክተዋል።
የተገልጋይን እርካታ ለማሳደግም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነት ላይም በስፋት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተሰሩት ከ90ሺህ በላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት በህዝብ ተሳትፎ መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው፥ ዞኑ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን ወደ አንድ ማእከል የማምጣትና በቴክኖሎጂ የማደረጀት ተግባር ማከናወኑን አንስተዋል።
የዚሁ አካል የሆነው አዲሱ የዞኑ አስተዳደር ህንፃም ለተገልጋዮች ምቹ ከመሆኑ ባለፈ አስተዳደሩ ያወጣ የነበረን ኪራይ መቅረፍ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ይህም 17 መስሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ የያዘ ከመሆኑም ባለፈ ከወረዳዎች ጋር በቴክኖሎጂ የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
ህንፃው ቤተ መጻሐፍት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የህፃናት ማቆያ፣ የተሽከርካሪ ማቆሚያና ሌሎችን የያዘና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደራጀ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በዚህም የዲጂታል አገልግሎት ለማቀላጠፍ የሚያስችል ምቹ የመስሪያ ቦታ መገንባቱን ገልጸዋል።
በምረቃው ፕሮግራም ላይ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የስራ ሃላፊዎች፣ አባገዳዎችና ሃደ ሲንቄዎች እንዲሁም ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።