ቀጥታ፡

በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው

ድሬደዋ፣ ግንቦት 15/2018 (ኢዜአ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ። 

የባለ 6 ወለል ህንፃ ግንባታን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ኃይለብርሃን ዜና አስጀምረዋል።

በወቅቱም የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደገለፁት፤ ኮርፖሬሽኑ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው።

ኮርፖሬሽኑ በድሬደዋ የመኖሪያ እና የንግድ ሞሎችን ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸው ስራዎች አበረታች በመሆናቸው ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል። 

የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኃይለብርሃን ዜና በበኩላቸው፤ ኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመሰረቱ ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እንደተመዘገበባቸው መሆኑን አመልክተዋል። 

ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ እየተመዘገቡ የሚገኙ የዘርፉ ለውጦችን በድሬዳዋ ለመድገም ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ 13 ህንፃዎችን ለመገንባት ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በዛሬው ዕለት የተከናወነው የህንፃ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው የኮርፖሬሽኑ 50ኛ ዓመት ምስረታ የማጠቃለያ በዓል በቀጣዩ ሰኞ በድሬዳዋ እንደሚከበርም አስታውቀዋል። 

 ኮርፖሬሽኑ በቤቶች ልማት ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ በማምጣት ችግሮችን በላቀ ደረጃ እየፈታ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በኮርፖሬሽኑ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እውነቱ ወርቅነህ ናቸው። 

 ኮርፖሬሽኑ  የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሩን ገልፀው የዚሁ ክብረ  በዓል ቀጣይ ክፍል በድሬዳዋ ከግንቦት 10/2018 ዓ/ም ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል ብለዋል። 

በ8 ሺህ 500 ካሬም ሜትር ስፋት ላይ የሚገነባው ዘመናዊ ህንፃ ለንግድ፣ ለመዝናኛ እና ለቢሮ አገልግሎቶች የሚውሉ የተለያዩ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑም በስነ-ስርዓቱ ላይ ተመላክቷል። 

በስነ-ስርዓቱ ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አብዲ ሙክታር እና ሌሎች የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የኮርፖሬሽኑ ምክትል ስራ አስፈፃሚዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም