ቀጥታ፡

ሰው ተኮሩ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ዘርፈ-ብዙ እፎይታ እየሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦ ሰው ተኮሩ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ዘርፈ-ብዙ እፎይታ እየሰጠ መሆኑን ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡ 

በአዲስ አበባ የተገነቡት የምገባ ማዕከላት መንግስት ለሰው ተኮር ልማት የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያሳያሉ።

ማዕከላቱ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን፣ የከፋ የጤና ችግር ያለባቸውንና ጧሪ የሌላቸውን አረጋውያን በቋሚነት በየዕለቱ በመመገብ ላይ ይገኛሉ።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ቁጥር 20 የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል በቀን 500 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ምገባ ያከናውናል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የማዕከሉ ተጠቃሚ እርቄ መኩሪያው፤ በተቋሙ አማካኝነት የዕለት ጉርሳቸውን ያለመቸገር እያገኙ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት ለዜጎቹ የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍና እንክብካቤ በእጅጉ አድንቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የምገባ ማዕከሉ በተለይም በከፍተኛ የኑሮ ውድነትና ጫና ውስጥ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትልቅ እፎይታን የሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው ተጠቃሚ እናኒ ካሰይ በበኩላቸው፤ ከማዕከሉ የተመጣጠነ ምግብ እያገኙ መሆኑን ጠቅሰው፤ የከተማ አስተዳደሩ ይህንን መሰል በጎ ተግባር በማከናወኑ ሊመሰገን ይገባዋል ብለዋል።

በምገባ ማዕከሉ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሰረት ጉታ እና የሺ ብርሃኔ የራሳቸውን ኑሮ ዘላቂ በሆነ የገቢ ምንጭ መደገፍ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ማዕከሉ ከፈጠረላቸው የተሻለ የገቢ ዕድል ባሻገር፣ በየዕለቱ አቅመ ደካማ ወገኖቻቸውን በቅርበት ማገልገላቸው ትልቅ ሰብዓዊና የመንፈስ እርካታ እንዳጎናጸፈላቸውም ገልጸዋል።

በርካታ የሥራ ፈላጊ ማኅበረሰብ ክፍሎች አዲስ ተስፋና የተረጋጋ የሕይወት መሠረት እየጣለ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በመሆኑም መሰል ሰው ተኮር ማዕከላት መስፋፋታቸው በየአካባቢው ያለውን የሥራ አጥነት ጫና ለመቀነስና ማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለው ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል።


 

የአዲስ አበባ የምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ስንታየሁ ማሞ እንዳሉት፤ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለወላጅ አልባ ሕፃናትና ለሀገር ባለውለታ ዜጎች አለኝታነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው።

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በሚገኙ 29 የምገባ ማዕከላት ለተጠቃሚዎች ንጹህና የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ይህ ሰው ተኮር ሥራ ስኬታማ ሊሆን የቻለው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ባለሀብቶች እንዲሁም በጎ ፈቃደኛ ዜጎች ለፕሮግራሙ እያበረከቱ ባለው ቀና ድጋፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።

መርሐ-ግብሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባለፈ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የመደጋገፍና የመረዳዳት ባህልን እንዲሁም ማኅበራዊ መስተጋብርን በእጅጉ ያጠናከረ መሆኑንም ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም