ቀጥታ፡

ጠቅላላ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች በንቃት ሊሳተፉ ይገባል   

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 15/2018(ኢዜአ)፦7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት እናታለም እንዳለ ገለጹ፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር "በፖለቲካ፣ በምርጫና ሰላም ግንባታ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ማጎልበት" በሚል መሪ ሃሳብ ከማህበሩ አባላት ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት እናታለም እንዳለ በዚሁ ወቅት፤ ማህበሩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና እኩል ተሳታፊነትን የማረጋገጥ ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሴቶች የመምረጥና የመመረጥ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የሚያግዙ የአቅም ግንባታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 2 ሺህ 200 የማህበሩ አባል የሆኑ ሴቶች ሰልጥነው የታዛቢነት ፍቃድ መውሰዳቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሌሎችም ዕድሜያቸው ለምርጫ የደረሱ የማህበረሰብ ክፍሎች በምርጫው በመሳተፍ  የሚመራቸውን መንግስት በድምፃቸው መምረጥ እንዲችሉ የማስገንዘብ ስራ እያከናውኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም ሴቶች በሃገር ሰላምና ፖለቲካ ውስጥ ያላቸውን የላቀ ፋይዳ በመገንዘብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሴቶች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።


 

የህብረተሰቡ ግንዛቤ ለማሳደግ ቤት ለቤት በመሄድና የተለያዩ መርሃግብሮችን በማዘጋጀት ለምርጫው አሳታፊነት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት የማህበሩ አባል ወይዘሮ መሰረት ሶርሳ ናቸው።

ወይዘሮ አዳነች አሉላ በበኩላቸው፤ ለምርጫ የደረሱ ዜጎች ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ በማስተማር የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ከ513 ሺህ በላይ አባላት እንዳለው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም